ለጂንካ ማረሚያ ፖሊስ ተቋም ከ90 ሺህ ብር በላይ ዋጋ ያላቸው መጻሕፍት በስጦታ ተበረከቱ።
ጷጉሜ 2/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት በመላ ኢትዮጵያ በመዘዋወር እያካሔደ የሚገኘው "የንባብ ባህል ለትምህርት ጥራት!" ንቅናቄ ዛሬ ጳጉሜ 2/2017ዓ.ም በጂንካ ማረማያ ፖሊስ ተቋም መካሔዱን ቀጥሏል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የማረምና ማነጽ ተሀድሶ ልማት ዲቪዥን ኃላፊ ኮማንደር ደመቀ እንዳለ የጂንካ ማረሚያ ቤት 600 በላይ ታራሚዎችን፥ በአካባቢው ከሚገኙ አቅመ ደካማ የሕብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ ከ50 በላይ ሕፃናትን እንደሚያስተምር ገልጸው ለመማር ማስተማር ሒደቱ ትልቁ ችግር የነበረው ከመሐል ሀገር የራቅን እንደመሆናችን የመጻሕፍት እጥረት ነው ብለዋል፡፡
ለዚህም ዛሬ የተደረገው ድጋፍ ይበልጥ ለመስራት እንደሚያግዝ ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት የስራ አመራር ስራ አስፈጻሚ አቶ አብነት አበራ በበኩላቸው ዛሬ ጷጉሜ 2 በሕብር ቀን ብዝሐ ሕዝብ ባለባት በጂንካ ከተማ በመገኘታችን ደስተኞች ነን ብለው ማረሚያ ቤት ብዙ ታላላቅ ሰዎች የሚወጡበት ተቋም እንደመሆኑ በቆይታችሁ መጻሕፍት የማንበብ ባህል አዳብራችሁ መልካም ተፅዕኖ መፍጠር ትችላላችሁ ሲሉ መክረዋል፡፡
በመርሐግብሩ ስነ ፅሑፍ ላቀረቡ ታሪሚዎች የመጽሐፍት ሽልማት ተበረክቷል።
የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ለጂንካ ማረሚያ ፖሊስ ተቋም ከ90 ሺህ ብር በላይ ዋጋ ያላቸው 300 መጻሕፍትን የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት የስራ አመራር ስራ አስፈጻሚ አቶ አብነት አበራ ለኮማንደር ደመቀ እንዳለ በስጦታ አበርክተዋል።