የ2018 አዲስ ዓመት ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ ካርዶችን ለሰራተኛው በመስጠት አዲሱን ዓመት ተበስሯል፡፡

መስከረም/2018 ዓ.ም 

የ2018 አዲስ ዓመት ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ ካርዶችን ለሰራተኛው በመስጠት አዲሱን ዓመት ተበስሯል፡፡

“መስከረም ተፈጥሮም ራሷን የምታድስ ከሆነ እኛም ቆም ብለን ራሳችንን ለማየትና ለመረዳት ጥሩ ጊዜ ነው፡፡”(የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሠርፀ ፍሬስብሀት)

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ነፊሳ አልማህዲ የ2018 አዲስ ዓመት በግል፣በቡድንና በተቋም ደረጃ አቅደን ያልተሳካልን እንዲሁም ደግሞ በሀገር ደረጃ ይሁን ብለን ተመኝተን ያልተሳካልንን በ2018 ላይ እንዲሳካልን በማለት ተመኝተው

አክለውም በሀገራችን የምንመኘው ሰላም ወርዶልን ከህዳሴ ግድብ በተጨማሪ ስለ ወደባችን ደግሞ እያሰብን ስለሆነ የቀይባህር ጥያቄ የራሳችን አድርገን፤አጀንዳም ቀርጸን እና እዛ ላይ በጋራ ተወያይተን  በህዳሴው ዳግም አድዋን እንደደገምን ሌላ አድዋን የምንደግምበት ጊዜ እንዲሆንም ተመኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሠርፀ ፍሬስብሀት በእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው በግዜ ሂደት ውስጥ የማይለካ የማይፈተሸ ነገር የለም፤ በግዜ ዑደት ውስጥ የሚመጣው አዲስ ዓመት የሰለቸን የማደስ፣ የመረረን የማጣፈጥ ትልቅ ችሎታ አለው ብለው ኢትዮጵያ ተፈጥሮና የግዜ ቀመር ተስማምተው እውነት ዘመን ተቀይሯል የሚሉበት ሀገር እንደሆነች የአደይ አበባንና የመስቀል ወፍን አመላካችነት ገልጸው ተናግረዋል፡፡

አክለውም በመስከረም ተገናኝቶ ውብ ሃሳብ ተለዋውጦ ዓመቱ የሰላም ይሁንልን ብሎ ስራን መጀመር በጣም ደስ የሚል ስሜትን እንደሚፈጥር ተናግረው የምንሸምትና የምንሰፍረውን እቃ ልኬት ውስጥ ገብቶ እንደሚሰፈር እኛም የሰራነው ስራና የህይወታችን ረብህ ይለካል፤ ስለዚህ ምን ረብህ አተረፍን በህይወታችን ውስጥ ምን የሚበጅ ስራ ሰራን በተቋማችንና በሀገራችን ውስጥ የእኛ አስተዋጽዖ የትኛው ነው የሚለውን የሚያስለይ፣ የሚያስለካና የህይወት ሚዛን ውስጥ የሚከተን ጊዜ የሚባለው መመሪያ ነው ብለዋል፡፡

በ1946 ዓ.ም አካባቢ በአንድ ግለሰብ (በአቶ ታደሰ ታቼ) የኢትዮጵያ ህዳብ ግድብን እንዴት መገንባት እንደሚቻል በወቅቱ ለነበረው የመዘጋጃ ኃላፊ የተጻፈ ደብዳቤን መነሻ በማድረግና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከተቋሙ ጋር ያለው ቁርኝትና መዛግብቱም በተቋማችን ተጠብቆ እንደሚገኝ ጠቁመው በሀገራችን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ያቀድናቸውና የጀመርናቸው የልማት ስራዎች በግዜ ፍጥነት ተጠናቀው አገልግሎት እየሰጡም እንደሚገኝ በአዲስ ዘመን መባቻ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አንዱ ማሳያም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም  በክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ወ/ሮ ነፊሳ እጅ ለአጠቃላይ የተቋሙ ሰራተኞችና ስራ አስፈጻሚዎች የአዲስ ዘመን ማብሰሪያ የተዘጋጀ የእንኳን አደረሳችሁ ካርድ ተበርክቶላቸዋል፡፡

Share this Post