በሕትመት ውጤቶች አሰባሰብና በአዋጅ ቁጥር 179/91 ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ ተካሄደ

ግንቦት 13/ 2018 ዓ.ም አዲስ አበባ

የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት አሳታሚዎች፣ደራስያን፣የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣የመንግሥትና የግል ተቋማት ተወካዮች እና የተለያዩ ማህበራት በተገኙበት የሕትመት ውጤቶችን ማሰባሰብና በአዋጅ ቁጥር 179/91 አፈጻጸም ዙሪያ ያተኮረ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ የምክክር መድረክ አካሄደ።

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት በመድረኩ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ "የተቋማችን ማንነት የቆመው እናንተ የፈጠራ ውጤት ውስጥ፣ እናንተ አእምሮ ውስጥና እዚህ ይቀመጥልን ብላችሁ በምታስቀምጡት ሀብት ላይ ነው" በማለት የባለሙያዎችንና የባለድርሻ አካላትን አስተዋጽኦ አጉልተዋል።

የመረጃ ሀብቶች አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ስለሺ ሽፈራው በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የራሷ ፊደልና ጥልቅ የሥነ-ጽሑፍ ታሪክ ቢኖራትም እስካሁን የተሰባሰቡ የሕዝብ የአእምሮ ሀብቶች ካለን እምቅ አቅም አንጻር በቂ እንዳልሆኑ ገልጸዋል። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት በአዋጅ ቁጥር 179/91 የተቀመጠው የሕትመት ውጤቶችን ለብሔራዊ ቤተ-መጻሕፍት የማስረከብ ግዴታ በተሟላ ሁኔታ ተፈጻሚ አለመሆኑን ጠቁመዋል።

በመድረኩ ላይ አዋጅ ቁጥር 179/91 በደራስያንና አሳታሚዎች ላይ ጫና ለመፍጠር ሳይሆን፡-

የቅርስና የፈጠራ ባለቤትነትን ለማረጋገጥ፣

ፍትሐዊና ማዕከላዊ የመረጃ ተደራሽነትን ለመፍጠር፣

የዲጂታል ሕትመቶችን በማካተት የሀገሪቱን የዕውቀት ሀብት ሙሉ በሙሉ ለመመዝገብ የታለመ እንደሆነ ተብራርቷል።

የኦዲዮ ቪዥዋል ቅርስ ጥበቃ እና በሕግ ሥርዓት የማስቀመጥ ጠቀሜታ በአቶ ሠርፀ ፍሬ ስብሐት፣ ዲበ ውሂብ፡ ለሕትመት ጥራት እና ተደራሽነት በዶ/ር ደርብ አዶ፣ እንደዚሁም የመረጃ ሀብቶች አሰባሰብ ሥርዓት ከአዋጅ 179/1991 አኳያ በአቶ እስራኤል በዙ የቀረቡ ጥናታዊ ጽሑፎች ለውይይቱ መነሻ የሆኑ ሲሆን፤ ተሳታፊዎችም ተቋሙ ሥራዎቹን ይበልጥ ማስተዋወቅ እንዳለበት፣ የአዋጁ ተፈጻሚነት እስከ መጨረሻው የሕግ አግባብ መከተል እንደሚገባውና መሰል መድረኮች በቋሚነት እንዲቀጥሉ ምክረ-ሐሳብ አቅርበዋል።

በመጨረሻም ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሠርፀ ፍሬ ስብሐት እንደገለጹት ተቋሙ የኢትዮጵያን የ2030 የዲጂታይዜሽን ግብ ለማሳካት ከኢኖቬሽንና ሳይንስ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ዘመናዊ የዲጂታይዜሽን ማሽኖችን አስገብቷል። ይህም በተቋማችን የሕትመት ውጤቶችን ዲጂታይዝ የማድረግ ሰፊ ስራ ሲጠናቀቅ ጥበበኛው ሥራውን መስጠት ብቻ ሳይሆን ከሥራው መጠቀም የሚያስችለውን አሠራር ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።

Share this Post