የካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ በዓል በፓናል ውይይት ተከበረ፡፡
እንደ ሀገር ለ89ኛው ጊዜ ታስቦ የዋለው የካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ በዓል የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት፣በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም፣ከዕዝራ ሱቱኤል የጥናትና ምርምር ማዕከል እንዲሁም ከጥንታዊው የተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በጋራ በተዘጋጀ መድረክ ቀኑን አስመልክቶ የፓናል ውይይት በማካሔድ አክብሯል፡፡
በፓናል ውይይቱ የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር ዶ/ር ዮሐንስ አድገህ፣ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፣ የዕለቱ የክብር እንግዳ የጀግኖች አርበኞች ማኀበር ሊቀመንበር ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ተወካይ እና የማህበሩ ሥራ አመራር ጥላሁን ጣሰው፣ስለታሪኩ በርካታ መጻሕፍት የጻፉት ፕሮፌሰር ኢነ ካምፕቤል፣ የተከበሩ አምባሳደር ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን፣ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች፣ የኢፌድሪ መከላከያ ሰራዊትና የፖሊስ አባላት፣ሚዲያና ጥሪ የተደረገላቸው በርካታ ተሳታፊዎች የተገኙበት ነበር፡፡
በዝግጅቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት ነፃነትን ተንከባከቧት እውነት ራሷን ትጠብቃለች፤ነፃነት በሌለበት የተገለጠች እውነት ራሷን ታጠፋለች በማለት ተናግረው ዛሬ በነፃነት አንገታችንን እንዳንደፋ ያደረጉ አባቶቻችን ያስረከቡንን ታላቅ ሀገር ለጠላት አሳልፈን ባለመስጠት የድርሻችንን መወጣት እንዳለብን ተናግረዋል፡፡
በዕለቱም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር ዶ/ር ዮሐንስ አድገህ እና የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ቀኑን በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የዕዝራ ስቱኤል የጥናትና ምርምር ማዕከል መሥራች አቶ ዕዝራ ንጋቱ የዕለቱን መርሐ ግብር በማስመልከት ንግግር ሲያደርጉ የአገር ነፃነት በወርቅ በብርና በዕንቁ የሚገበይ ሳይሆን በስራ በድካምና በደም የሚገዛ የከበረ ህይወት ነው ብለዋል።
የዕለቱ የክብር እንግዳ የጀግኖች ማኀበር ሊቀመንበር ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ተወካይ እና የማህበሩ ሥራ አመራር ጥላሁን ጣሰው በዓሉ ለምን ታስቦ እንደሚውልና እንዴት እንደሚከበር ሲገልጹ ግፉ፦ የፋሺስት ወታደሮች እና ባንዳዎች የየካቲት 12 ተጎጂዎችን በጥይት፣በአካፋ እና በዶማ መጨፍጨፋቸው በታሪክ ተመዝግቧል፤መታሰቢያ፦ ይህ ቀን በየዓመቱ የካቲት 12 በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ በሚገኘው የሰማእታት ሐውልት መታሰቢያ የአበባ ጉንጉን በማኖር እና የሐገር ፍቅር ጽናትን በማሰብ እንደሚከበር እና ዓላማ፦ ቀኑ አባቶቻችን ለሀገራቸው ነፃነት የከፈሉትን መስዋዕትነት ለመዘከር፣ የሰማእታቱን አልገዛም ባይነት ጽናት ለመዘከር እና አሁን ያለውን ትውልድ ሀገሩን እንዲጠብቅ ለማስተማር እንደሚውልም ተናግረዋል፡፡
የካቲት 12 ቀን በ1929 ዓ.ም የፋሺስት ኢጣሊያ ወታደሮች በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ ያደረሱትን ዘግናኝ ጭፍጨፋ የምናስብበት የሰማእታት ቀን መሆኑን በወቅቱ የጣሊያን ምሥራቅ አፍሪቃ ገዢ የነበሩት ሮዶልፎ ግራዚያኒ ላይ በተፈጸመው የግድያ ሙከራ ተበቅለው፣ ለሦስት ቀናት ባካሄዱት የዘፈቀደ ጭፍጨፋ ከ30,000 በላይ ንጹሐን ኢትዮጵያውያን የተገደሉበትን የሚያሳይ የመነሻ ጽሑፍ በታሪክ ተመራማሪው ዲያቆን ተረፈ ወርቁ ለውይይት ቀርቦ ከተሳታፊዎች ሃሳብ አስተያየት ተሰጥቶበታል፡፡
በመጨረሻም ለእይታ የተዘጋጀ የሥዕል ኤግዚቢሽን ተጎብኝቶ ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡