ሙያዊ ዕውቀትን በመጠቀም ዘርፉና ማሻሻል እንደሚገባ ተገለጸ

የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት የአብያተመዛግብትና አብያተመጻሕፍት ጥናትና ምርምር ስልጠና ዳይሬክቶሬት ሁለተኛ ዙር መደበኛ ስልጠና ከመስከረም 23/2015 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥቅምት 11/2015 ዓ.ም በቤተመጻሕፍት ሙያዊ ሳይንስ ዙሪያ ሲሰጥ የነበረው ተከታታይነት ያለው ስልጠና ተጠናቋል፡፡

ስልጠናው ከኦሮምያ እና አዲስ አበባ ሆኖ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እንዲሁም ከሐይማኖት ተቋማት ለተውጣጡ በሙያው ላይ ለሚሰሩ ባለሙያዎች የተሰጠ እንደሆነም ስልጠናውን ሲሰጡ የነበሩት በኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት የቤተመጻሕፍት ሙያ ሳይንስ ስልጠናና ምክር ቡድን መሪ አቶ እስራኤል በዙ ተናግረው በስልጠናውም ወንድ 14 ሴት 16 በጥቅሉ 30 ሰልጣኞች እንደተሳተፊ ተናግረዋል፡፡

አሰልጣኙ አቶ እስራኤል ስልጠናው ያተኮረው ካታሎጊንግ፣ ክላሲፊኬሽንና ዲጅታል ላይብረሪ ላይ እንደሆነና አስፈላጊነቱን በተመለከተም በሀገሪቱ ውስጥ በቤተ-መጻሕፍት ሙያ ዙሪያ ተመራቂ ባለመኖሩ ያለውን የቤተ-መጻሕፍት ሙያ ሳይንስ ክፍተት ለመሸፈን እንደሚረዳም ተናግረዋል፡፡

በዕለቱም የአብያተመዛግብትና አብያተመጻሕፍት ጥናትና ምርምር ስልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ከፋለ በምርቃቱ ላይ ተገኝተው የስልጠናውንም ዓላማ ሲናገሩ ስልጠናውን የሰለጠናችሁት የቤተመጻሕፍት ባለሙያዎች እንደመሆናችሁ የዘርፉን ሙያ አውቃችሁ በተወሰነ ደረጃ በሙያ ላይ የተመሰረተ ስራ እንድትሰሩ ለማስቻል ነው ብለዋል፡፡

በመጨረሻም አቶ መኮንን ስልጠናውን ላጠናቀቁ ሰልጣኞች ከአገልግሎቱ የተዘጋጀውን የምስክር ወረቀት አበርክተው ከሰልጣኞች ሐሳብ አስተያየት ተሰጥቶ ስልጠናው ተጠናቋል፡፡

Share this Post