የኢትዮጵያ ታሪክንና ጥበብን ባሟላ መልኩ የተጻፈ መጽሐፍ ተመረቀ
የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት “Disabilities, Rehabilitation and the society of Twentieth Century Ethiopia,History perspective” በሚል በእንግሊዘኛ ቋንቋ ለንባብ የበቃው የዶክተር ሲሳይ ብርሃኔ የዶክተሬት ድግሪ ማሟያ ጽሑፍ የሆነውንና ለመጽሐፍትነት የበቃውን ለሀገራችን አይነስውራንና አካል ጉዳተኞች ተስፋ እንዳይቆርጡ ጥንካሬ ሊሆን የሚችል መጽሐፍ ጥቅምት 2/2014 ዓ.ም በፍሬንድ ሺፕ ሆቴል ታላላቅ ሰዎች በተገኙበት አስመርቋል፡፡
በመጽሐፍት ምርቃኑ ላይም መጽሐፉ ለአንባቢን እንዲደርስ የአንበሳውን ሚና የተጫወቱትና የጠንካራ ሴት ተምሳሌት የሆኑት የዶ/ር ሲሳይ ባለቤት ወ/ሮ ፍቅርተ ጥበቡ፣የማህበረሰብ ጥናት አጥኚው ዶ/ር አሉላ ፓንክረስ፣የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ፣ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ አሳልፈው አህመዲን፣ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞችና አይነስውራን ማህበር የስራ ኃላፊዎችና ተወካዮች እና ጥሪ የተደረገላቸው በርካታ እንግዶች ታድመዋል፡፡
የመጽሐፉ ጸሐፊ ይቺን ታላቅ ቀንና የልፋታቸውን ውጤት በሕይወት ኖረው ለማየት ባይታደሉም ዶ/ር ሲሳይ በርካታ ጊዜያቸውን ካሳለፉበት የሰበታ አይነስውራን ማህበር ጀምሮ ሕይወታቸው እስካለፈችበት ጊዜ ድረስ የትዳ አጋራቸው ወ/ሮ ፍቅርተ ጥበቡ እና የሚያውቋቸው የቅርብ ጓደኞቻቸው እንደተናገሩት ለሀገራቸው በርካታ ታሪክ የማይረሳው ስራዎችን የሰሩና በርካታ ለሀገር ጠቃሚ ሰዎችን ያፈሩ፣በሕይወት በነበሩበትም ወቅት ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር የስራና ማህበራዊ ግንኙነታቸው ጠንካራ እንደሆኑ፤ በተመደቡበት የሙያ መስክ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የሚወጡ እና የሀገር ባለውለታ እንደሆኑ፤ለትዳራቸው ታማኝና ለውጥን ከትዳራቸው በመጀመር የትዳር አጋራቸውን በልጅነት እድሜያቸው አግብተው በማስተማር የማስተርስ ድግሪያቸውን እንዲይዙ ያደረጉ ጠንካራ አባወራም እንደሆኑ በትዳር አጋራቸው የተመሰከረላቸው ሲሆኑ አሁን የጻፉት መጽሐፋቸው ለአይነስውራንና ለአካል ጉዳተኞች ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ በሚገቡበት ወቅት የመጀመሪያ ኮርስ ሊሆን የሚችል ስራን በመጽሐፍ መልክ ያቀረቡ የሀገር ባለውለታ እንደሆኑም ከቅርብ ጓደኞቻቸውና በስራ አጋጣሚ ከተገናኟቸው የቅርብ ሰዎች ለታዳሚዎች ቀርቧል፡፡
በዝግጅቱም በገጣሚ አለኸኝ ሽፈራው፣በገጣሚ ሰለሞን ሳህለ ያ’ፍቃሪ ሰው ትንፋሽ ከሚለው የግጥም መድብሉ ላይ አስተማሪ ግጥም በራሱ በገጣሚው ወቅታዊ ግጥም ሲቀርብ፡፡በደራ ገዛኸኝ ሀብቴ ወግ በአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር በአቶ ይኩኖአምላክም ከደራሲ መዘክር ግርማ የግጥም መድብል የዶ/ር ሲሳይ የትዳር አጋርንና ከጠንካራ ወንድ ጀርባ ያለች ሴትን ጥንካሬ ሊያወድስ ይችላል ያሉትን የግጥም ስንኝ ለታዳሚው አንብበው ለወ/ሮ ፍቅርተም ሰው ሆነሽ ወዳለፈው ሳይሆን ወደሚመጣው ሕይወትሽ ቀጥለሽ አዘንሽን ቆርጠሸ ለመበረታታት ሞክሪ በማለት መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል፡፡
መጽሐፉንም በተመለከተ የኢትዮጵያ ታሪክንና ጥበብን ባሟላ መልኩ የተጻፈ መጽሐፍ በመሆኑ በተለይ የታሪክ ማህበራዊ ሳይንስ ምርምርን እንደሚያጠናክር እና አካል ጉዳተኞችን በሚመለከት እንደ መጀመሪያ ኮርስ በዩኒቨርሲቲዎች እንዲሰጥ ሲጠቆም በዶ/ር አሉላ ፓንክረስም ዶ/ር ሲሳይ ይህንን መጽሐፍ ሲጽፉ ትልቅ ድካም የተደከመበት እንደሆነ ከይዘቱ መረዳት እንደሚቻል ተናግረው አክለውም መጽሐፉ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ብቻ ሆኖ መቅረት እንደሌለበት መጽሐፉ በተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ለአንባቢ መቅረብ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
በዕለቱም የአዳማ ዩኒቨርሲቲ ሰራተኞችና አመራሮች የዶ/ር ሲሳይ ስራው ህያው ሆኖ ለዚህ በመድረሱ ምስጋና ለባለቤታቸው ለወ/ሮ ፍቅርተ ጥበቡ ሲሰጡ የዩኒቨርስቲው አስተዳደር ክፍልም መጽሐፉን ለአንባቢው ለማድረስ ለመረከብ ቃል መግባቱም ተጠቁሟል፡፡
በመጨረሻም መጽሐፉን የዶ/ር ሲሳይ ባለቤት ወ/ሮ ፍቅርተ ጥበቡ፣የማህበረሰብ ጥናት አጥኚው ዶ/ር አሉላ ፓንክረስ እና የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ በጋራ በመሆን ለንባብ እንዲበቃ መርቀዋል፡፡