የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ነብይን በሀገሩ አከበረ

አንጋፋው ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ ተርጓሚና የጥበብ ሰው ነብይ መኮንን

• ነገም ሌላ ቀን ነው

• የእኛ ሰው በአሜሪካ

• የመጨረሻው ንግግር የተሰኙ ሶስት መጻሕፍት ከኢትዮጵያ ቤተመዛግብት እና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ጋር በመሆን ሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ በፍሬንድሺፕ ሆቴል ታላላቅ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ እንግዶች ፣ አድናቂዎችና ቤተሰቦቹ በተገኙበት በድምቀት ተመርቋል ።

በዚህ የመጻሕፍት ምረቃ ላይ የጋዜጠኛ ነብይ መኮንንን ስራዎች እና የራሳቸውን ስራዎች እንዲሁም ትውውቅና ጓደኝነታቸውን አስመልክቶ በመድረኩ ካቀረቡት መሀል ተፈሪ አለሙ፣ በኃይሉ ገ/መድህን፣ ጌትነት እንየው፣ ፍሬዘር አድማሱ፣ ሰለሞን ሳህለ፣ ተስፋሁን ፍራሽ አዳሽ፣ ምልዕቲ ኪሮስ፣ ነፃነት ወርቅነህ ዋንኞቹ ነበሩ።

በመርሐ ግብሩ መጽሐፉን የመረቁት ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ ተርጓሚና የጥበብ ሰው ነብይ መኮንን እና የኢትዮጵያ ቤተመዛግብት እና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ ሲሆኑ ደራሲው በአንድ ኢጣሊያዊ ሰዓሊ ፈረንሳይ ሀገር የተሰራ በልዩ መልክ ተቀርፆ የተዘጋጀ እና ልክ እንደ ብሬል ጽሑፍ በእጅ ሲዳሰስ ፊደሎቹ የሚነበቡ "ዋ" የተሰኘ የግጥም መድብሉ እና ጋዜጠኛ ነብይ መኮንን ከአቶ አሰፋ ጫቦ ጋር በእጅ ጽሑፍ የተለዋወጧቸው 36 ገፅ ደብዳቤዎቹን ለኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት እና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ለአቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ በስጦታ አበርክቷል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ "ይህ በወመዘክር/በኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ሲቀመጥ እኔ እዛ እንዳለሁ እቆጥረዋለሁ። ምንነቱ እና ዋጋውም ለሚገባው አካል እንደሰጠሁት አምናለሁ ።" ሲል ስለሰጠው ስጦታ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ የዚህን ታላቅ የጥበብ ሰው ስራዎች አዘጋጅ በመሆኑ ክብር እንደሚሰማውና በንባብ እና በስነ ጽሑፍ ስራዎች ላይ ደራሲያንን በመደገፍ ተሳትፎው እንደሚቀጥል አሳውቀዋል ።

 

Share this Post