"ንባብ ብቁ ሰው ያደርጋል!"በሚል መሪ ቃል ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፓናል ውይይት በይፋ ተከፍቷል።
ጥቅምት 27/2019 ዓ.ም ሀዋሳ ከተማ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ባለስልጣን "ንባብ ብቁ ሰው ያደርጋል!" በሚል መሪ ቃል ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ፤ ከሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ባህል ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር በሀዋሳ ከተማ የተዘጋጀው የንባብ ሳምንት፣ቡክፌር፣ ኤግዚቢሽን፣ ስልጠና እና የፓናል ውይይት መርሐ ግብር በይፋ ተከፍቷል።
በዝግጅቱም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት፣ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚ ጉዳዮች ም/ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ኢንጅነር ፍሰሃ ጌታቸው፣ታላላቅ ምሁራንና ደራሲያን ከባለስልጣኑ የሚመለከታቸው ሥራ አስፈጻሚዎችና ባለሙያዎች፣ የሚድያ አካላት፣ከተለያዩ ት/ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የከተማ ነዋሪዎች ታድመውበታል።
የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚ ጉዳዮች ም/ፕሬዘዳንት ዶ/ር ኢንጂነር ፍሰሃ ጌታቸው
የሰው ልጆች በዕውቀት እንዲያድጉ፣ ችግሮቻቸውን በሳይንሳዊ አቀራረብ እንዲፈቱ፣ ፈጠራን እንዲያበረታቱና ለለውጥ የሚያስፈልገውን አቅም እንዲገነቡ የንባብ ባህል ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
የዝግጅቱን ጥቅል ዓላማ ገለጻ ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት የንባብን ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ እና አስፈላጊነቱን በማብራራት ወቅቱ ለትውልዱ ከፍተኛ የንባብ ማነቃቂያ የሚፈልግ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ትውልድ የሚፈልገውን የዲጂታል ንባብ ማበረታታት ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመው ተቋሙም የዲጂታል ንባብ ባህልን ለማስረጽና ለማሳደግ በርካታ ታላላቅ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የሰው ሠራሽ አስተውሎት አጠቃቀም በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ መምጣቱን ያነሱት ዳይሬክተሩ ቴክኖሎጂው በዲጂታል ዘመን አስፈላጊ ቢሆንም፣ ለመረጃ ማግኛነት እንጂ ለጥናትና ምርምር እንደ ሙሉ ማረጋገጫ ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ
ንባብ የግለሰብን አድማስ ያሰፋል፣ የማህበረሰብን አስተሳሰብ ያዳብራል፣የሀገርንም የእድገት መሠረት ያጠናክራል።ስለዚህ ንባብን የግል ምርጫ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ ኃላፊነት አድርገን እንመልከተው መጻሕፍትን እናንብብ እውቀትን እናጋራ፣ሐሳብን እናበረታታ ቴክኖሎጂን በጥበብና በኃላፊነት እንጠቀም፣የሀገራችንን ታሪክና ባህል እንጠብቅ፣የራሳችንን ዕውቀት እናዳብር፣ለሚመጣው ትውልድም የንባብና የእውቀት ባህልን እናውርስ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በመርሐ ግብሩ በዶ/ር መልሰው ደጀኔ፣በዶ/ር አለማየሁ አረዳ ከሀዋሳ ከተማ ለተውጣጡ ተማሪዎች እና ለዝግጅቱ ታዳሚዎች ንባብን በማስመልከት ሰፊ ግንዛቤ ማስጨበጫ መልዕክቶች ሲተላለፉ፣ በክልሉ የባህል ኪነት ቡድንና ማርሽ ባንድ ሀገራዊ ይዘት እና ስለንባብ የሚያወሱ ሙዚቃዎች ሲቀርቡ፥
በአጠቃላይ ለአሥራ ሦሥት አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቤተመጻህፍት ቤቶች፣ለሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እና ለሀዋሳ ማረሚያ ተቋም በቁጥር ሦሥት ሺህ ሦሥት መቶ መጽሐፍት /3300/ በብር 1,496,505 የፈጁ መጻሕፍት ከባለስልጣኑ በስጦታ መበርከቱ ተጠቁሟል።
የተዘጋጀው የመጽሐፍት ሽያጭ ኤግዚቢሽንና መዛግብቱን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብት እና ቤተመጻሕፍት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር፣በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ም/ ፕሬዘዳንት፣በኢ/ያ ሳይንስ አካዳሚ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር፣በሲዳማ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ም/ኃላፊ ለታዳሚው ክፍት ተደርጎል።