የተቋም አቅምን ከፍ ለማድረግ ተቋማዊ ህብር ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ሰኔ 15 / 2018 ዓ.ም አዲስ አበባ
በአራተኛው "እንገናኝ እንሰናኝ!"የሰኞ ንጋት የሠራተኞች መድረክ በተቋማዊ ህብር እና የጋራ ዓላማ ላይ አትኩሮት የሠጠ ውይይት ተካሔደ፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት በየሁለት ሳምንቱ ሰኞ ንጋት "እንገናኝ እንሰናኝ!" በሚል ስያሜ ምቹ የስራ አካባቢን እና መልካም የስራ ባልደረቦች ግንኙነትን በመፍጠር ተቋማዊና ሀገራዊ ራዕይ እና ተልዕኮን ለማሳካት በማለም የተጀመረው የማነቃቂያ መድረክ መርሐ ግብር ተካሒዷል።
በመድረኩ ሀሳባቸውን ለማካፈል የተገኙት እንግዳ የአሻም ሬድዮ ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ፣የጥበብ እና የዲስኩር መድረኮች አዘጋጅ፣የፎክሎርና የሥነ-ጽሑፍ እንዲሁም የሥነ መለኮት አጥኚና ተመራማሪ በተጨማሪም የምስክር ጌታነው ሚዲያና ፕሮሞሽን ባለቤት አቶ ምስክር ጌታነው ናቸው።
አቶ ምስክር ተቋሙንና በተቋሙ አገልግሎት የሚሰጡትን ሁሉ እንደ አንድ ዜጋ ለማመስገን እድሉን በማግኘታቸው መደሰታቸውን በመግለጽ ይህን ታሪካዊ ተቋም አቅሙን ከፍ ለማድረግ ተቋማዊ ህብር ወይም organizational harmony  ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።
በማብራሪያቸውም ተቋሙ ሊደርስበት ላሰበው ግብ ሁሉም የተቋሙ ባልደረባ እኩል ግንዛቤ እና የጋራ ዓላማ (unity of purpose) ሊኖረው እንደሚገባ እና ሁሉም የተቋሙ ባልደረባ በሚና ቢለያይም በአስፈላጊነት ግን እኩል መሆኑን (mutual respect) በመረዳት የእኔ መኖር ለተቋሙ አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ የሌላውም መኖር አስፈላጊ ነው የሚለውን መርህ መከተል እንደሚገባ ከተጨባጭ ነባራዊ ዕለት ተዕለት ሁኔታዎች ጋር በማያያዝ አስረድተዋል።
የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰርፀ ፍሬ ስብሐት በበኩላቸው የአቶ ምስክርን ሀሳብ በማጠናከር ህብር ፈጥሮ በአንድ ተቋም ውስጥ መስራት እንደ ግለሰብ፣እንደ ተቋም፣እንደ ሀገር ውጤታማ እንደሚያደርግ አስገንዝበዋል።
በማጠቃለያ ንግግራቸውም ያልተገባ ግላዊ ህልም ብዙ እንደሚያሳጣ እና ብዙ ዋጋ እንደሚያስከፍል አስረድተዋል።

Share this Post