አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት ከብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ጋር በመዛግብት አጠባበቅ ውይይት አረጉ።

የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት ከብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል ጋር የቤተክርስትያንዋ የጽሑፍ ቅርሶች እንዲሁም የድምጽና የምስል ሀብቶች ጠብቆ ለትውልድ ከማሻገር አንጻር ጥልቅ ውይይት አደረጉ።
ሰኔ 10/2018 ዓ.ም አዲስ አበባ
የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎትም ወደ ካቴድራሉ ሲያቀና ዓላማ ያደረገው እንደ ሀገር የተሰጠውን ስልጣንና ኃላፊነት ተግባራዊ በማድረግ የቤተክርስትያኗ መዛግብቶች ካሉበት ተሰብስበው በተቋሙ በቤተክርስቲያኗ ስም ስያሜ ቦታ ተሰጥቷቸው  ለተመራማሪዎች፣ለአንባቢያን ተደራጅተው እንዲቀመጡ በማድረግ እና ሰንዶ ለመጪው ትውልድ በማቆየት እንዲሻገሩ ለማስቻል እንዲሁም ከታሪክ ተጠያቂነት ለመዳን እንደሆነ አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት ለብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ በስፋት አስረድተዋል።
የይፋዊ ውይይቱ ዋነኛ ዓላማንም አቶ ሠርፀ ለብፁነታቸው ሲያስረዱ ሦሥት ትላልቅ ጉዳዮችን ዓላማ ያደረገ እንደሆነ አንደኛው የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት
ቤተክርስቲያንን ታሪካዊ መዛግብት፣መጻሕፍት፣ፎቶግራፎች፣ኦዲዮ ቪዥዋል ቅርሶች እና የኀትመት ውጤቶች በጋራ በመለየት ወደ ብሔራዊ ቤተመዛግብት በማምጣት ዘላቂ ጥበቃ እንዲደረግባቸው ማድረግ
በሁለተኛነት በቤተክርስቲያኒቱ የሥነ-መለኮት ዩኒቨርሲቲዎች እና በቅድስት መንበረ ቫቲካን ባለው የኢትዮጵያ ገዳም የሥነ መለኮት የሚካሔዱ የምርምር ሥራዎችን ለተመራማሪዎች እንዲደርሱ በማድረግ በብሔራዊ የዕውቀት ክምችት ማበልጸግ እና በ3ኛነት ኃላፊው ያቀረቡት ተቋሙ ካለው የረዥም ጊዜ ልምድ በመነሳት ለቤተክርስትያኑቱ የቤተመዛግብት እና ቤተመጻሕፍት ክፍል የቴክኒክ ድጋፍ እና ሥልጠና ለመስጠት ዝግጁ መኾኑን አስረድተዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል፣ ከኢትዮጵያ ቤተመዛግብት እና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በጽሕፈት ቤታቸው በነበራቸው የውይይት ጊዜ፣ የቤተክርስቲያኒቱን ጥልቀት ያለው ታሪክ በሰፊው አስረድተዋል። በተለይም፥ "የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ታሪካዊ ጉዞ እና የካቶሊክ ሃይማኖት በኢትዮጵያ ያለው ታሪክ ጥልቅ፣ ውስብስብ እና የኢትዮጵያን የፖለቲካና የባህል ታሪክ በቅርበት የተሳሰረ ነው።ፖርቹጊዞች የፕሪስተር ጆንን ሀገር ከመፈለግ ጉዟቸው፣ በተለይም ከፍራንሲስኮ አልቫሬዝ ጀምሮ በትልቅ ፍላጎት እና አድናቆት የታየች ሀገር ናት።  የካቶሊክ ሃይማኖት  በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በተለይም በ16ኛው እና በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከፖርቱጋልና ከስፔይን በመጡ ጄዝዊት ሚሽነሪዎች አማካኝነት ነበር።"ይላሉ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ።
በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የክሪስቶቫዎ ዳጋማ የጦር ሠራዊት መምጣት እና ከጦር ኃይሉ ጋር አብረው የገቡት የካቶሊክ ሚሽነሪዎች (ጄዝዊት)፣ እንደ ፔድሮ ፓኤዝ ያሉ ሚሽነሪዎች በጎርጎራ፣ በደንቀዝ እና በሌሎች የጎንደር አካባቢዎች አብያተ ክርስቲያናትን በመገንባት፣ የሕንፃ ጥበብን በማስተዋወቅ ትልቅ ተጽዕኖ ፈጥረው ነበር።"
"የካቶሊክ ሃይማኖት የአዲግራት እና የዓድዋ አካባቢ እንደ ፍሬሞና በመሳሰሉ ቦታዎች የካቶሊክ እምነት የትምህርት እና የሃይማኖት ማዕከል ኾነው አገልግለዋል። በተለይም በአሊተና እና በኢሮብ አካባቢዎች የካቶሊክ እምነት ከባህላዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ጎን ለጎን ተቀባይነትን በማግኘት፣ የራሱ የኾነ አሻራ ዐሳረፈ። የኤርትራው ከረንም የካቶሊክ ሚሽነሪዎች በጤና እና በትምህርት መስክ የገቡበት ትልቅ ማዕከል ነበር። በዘመኑ የነበረው የኅትመት ውጤቶች፣ እንደ እምኩሉ የካቶሊክ ማተሚያ ቤት ያሉ ተቋማት፣ ሃይማኖታዊ መጻሕፍትን በማሳተም ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።"
"በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሐረር ከተማ በአባ እንድርያስ ጃሮሶ አማካኝነት የተነሳሳው የካቶሊክ ሃይማኖት መንፈሳዊ መነቃቃት፣ ካቶሊካዊነት ከሰሜን ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ እንዲስፋፋ አድርጓል።"
"ኾኖም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ፈታኝ ወቅቶችን አሳልፋለች። የጣሊያን ወረራ (1928-1933 ዓ.ም.) አንዱ ወሳኝ ወቅት ነበር። ጣሊያኖች የካቶሊክ እምነትን ለፖለቲካ ዓላማቸው በመጠቀም፣ ከሌሎች አገራት የመጡ ሚሽነሪዎችን በማባረር፣ የራሳቸውን ጣሊያናዊ ሚሽነሪዎች ብቻ እንዲሰብኩ በማድረጋቸው በቤተክርስቲያኗ ላይ ጥላ ሆኖ ቀርቷል። በዚህ ሒደት ውስጥ፣ በተለይም የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አማኞች በሕዝብ ዘንድ ጥርጣሬ ውስጥ እንዲወድቁ የተደረገበት እና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እንደ "ወራሪ" መሣሪያ እንድትታይ የተደረገበት አስቸጋሪ ጊዜ ነበር።"
"የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በኢትዮጵያ የትምህርት ታሪክ ውስጥ ያላት አስተዋጽዖ ተወዳዳሪ የለውም። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (የቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ) ሲቋቋም የካቶሊክ ሚሽነሪዎች፣ በተለይም አሜሪካዊያኑ የኢየሱሳውያን አባቶች (Jesuits) የነበራቸው ሚና የመሠረተ ድንጋይ ዓይነት ነበር። የልደታ ካቴድራል እና ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት አካባቢ የተገነቡ ትምህርት ቤቶች ለሀገሪቱ የሰው ኃይል ግንባታ ትልቅ ድርሻ አበርክተዋል። የጤና ተቋማት፣ ሆስፒታሎች እና የሰብአዊ ተራድዖ ሥራዎች ቤተክርስቲያኗ እንደ ማኅበረሰብ ግንባታ ማዕከል እንድትታይ አድርገዋታል።"
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ታሪክ የኢትዮጵያ ታሪክ አካል ኾኖ በምርምር እና በጽሑፍ ተጠብቆ እንዲቆይ ማድረግ ብሔራዊ ግዴታ ነው። የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መሪ የኾኑት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል ይህንን ጉዳይ በሰፊው ያንፀባርቃሉ። ብፁዕ ካርዲናል እንደሚሉት፣ በዘመናት ውስጥ የተፈጠሩት የቤተክርስቲያኗ ታሪካዊ ሠነዶች፣ መጻሕፍት፣ የካርታ መረጃዎች፣ የሕክምና እና የትምህርት ተቋማት መዛግብት የኢትዮጵያ ሀብት ናቸው።
እርሳቸው እንደሚያስረዱት፣ እነዚህን አያሌ የታሪክ ማስረጃዎች በኢትዮጵያ ቤተመዛግብት እና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ውስጥ ተሰብስበው እና ተደራጅተው መቀመጣቸው የኢትዮጵያ ታሪክ ሙሉ እንዲኾን ያደርጋል። ይህ የትውልድ ቅርስ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን ሃይማኖታዊ ትግል ብቻ ሳይኾን፣ ለሀገር ግንባታ ያበረከተችውን አወንታዊ አስተዋጽዖ ለቀጣዩ ትውልድ በግልጽ ለማሳየት ያስችላል ብለዋል።
በመጨረሻም አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት ብፁዕነታቸው የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎትን እንዲጎበኙ በመጋበዝ እና የካቴድራሉን የአገልግሎት ክፍሎችን በመጎብኘት ተጠናቋል።

 

Share this Post