የሰኞ ንጋት «እንገናኝ እንሰናኝ» ሁለተኛውን የሠራተኞች መድረክ አገልጋይነትና በጎ ፈቃደኝነት

ግንቦት 17/ 2018 ዓ.ም አዲስ አበባ
በዛሬው የሰኞ ንጋት«እንገናኝ እንሰናኝ» መድረክ በበጎ ፈቃደኛው መሐመድ ካሳ አቅራቢነት አገልጋይነትና በጎ ፈቃደኝነት ከተቋማዊ አሰራር፣ከማህበራዊ እሴትና ከአለም አቀፋዊ ተሞክሮዎች አንጻር በስፋት ተዳሷል።
በማንኛውም ዘመንና ሁኔታ ኃላፊነትን መወጣት፣ በቃል የነበረውን በወረቀት፣ የወረቀቱን ዲጂታይዝ አድርጎ በብዙ ውጣ ውረድ መጠበቅ፣ ዕውቀትን ከመጥፋትና ከመረሳት ታድጎ ከትውልድ ጋር ማሰናኘት የተቋማዊ አገልጋይነት ዐብይ ጉዳይ እንደሆነ ተነስቷል።
የማህበራዊ እሴቶቻችን ለምሳሌ፦ የእርቅ ሥርዓቶች፣ የሐዘን የማርዳት ልማድ፣ እንግዳ ተቀባይነት፣ እንዲሁም የልምድ አዋላጆችና የወጌሻዎች ጥበብ የአገልጋይነት ትልቅ ማሳያዎች ናቸው። እነዚህ ተግባራት ማን እንዳደረገልን እስክንረሳ ድረስ ከታይታ በራቀ መልኩ በበጎነት የሚከናወኑ መሆናቸው ተብራርቷል።
በኢትዮጵያ ዓለም ስለ ሰብዓዊ መብት ማቀንቀን ከመጀመሩ በፊት የላቀ ሰብዓዊነት ይተገበር እንደነበር የአድዋ ጦርነትን በማጣቀስ ተገልጿል። በጦር ሜዳ የወደቁ የጠላት ወታደሮችን አስክሬን በሰብዓዊነት እስከ መቅበር፣ አልፎ ተርፎም ለቤተሰቦቻቸው የፍቅር ደብዳቤ በሚመስል ትሕትና የሐዘን መርዶ እስከ መላክ የደረሰ የላቀ ማንነት እንደነበረን ተወስቷል።
አገልጋይነት ለሰዎች የግል ስብዕና መቃናት፣ ለክህሎት ማደግና ለዕውቀት መበልጸግ የሌሎችን ምቾት ሳይነሱ የራስን አስተዋጽዖ ማበርከት ነው፤ ሁሌም በላጩ ሰው እንደሆነ ለሰዎች መልካም ነገርን በበጉ ፈቃደኝነት በመስራት ማሳየት አለብን የሚሉት በመድረኩ ትኩረት የተደረገባችው ርዕሰ ጉዳዮች ነበሩ።
በጎ ፈቃደኛ መሐመድ ካሳ ሰፊ የአገልጋይነትና የበጎ ፈቃደኝነት ተሞክሮ ያላቸው ሲሆን  ከነዚህም መካከል፦ በአፍሪካ የበጎ ፈቃደኝነት አምባሳደር በመሆን ማገልገላቸው፣ «ጥበብ ለተፈጥሮ» የሚል የአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚያተኩር ንቅናቄን መምራታቸው፣ በመላው ኢትዮጵያ ለወጣቶች የበጎ ፈቃደኝነት ስልጠና መስጠታቸውና የ«ጉዞ አድዋ» መስራቾች መካከል አንዱ መሆናቸው ይጠቀሳሉ።

Share this Post