የቻይና የትምህርት ዘርፍ ልዑካን በባህልና በእውቀት ላይ ከተቋሙ ጋር ለመስራት ገለጹ
ኢትዮጵያ እና ቻይና ቀደምት የሆነ የስልጣኔ ታሪክ ያላቸው እንደመሆናቸው ይህንን ስልጣኔ በእኩል እይታ በጋራ ማሳደግ እንዳለባቸው የገለጹት የቻይና የባህል እና የትምህርት ዘርፍ ልዑካን ግንቦት 14 ቀን2018 ዓ.ም ተቋሙን በጎበኙበት ወቅት ነው።በዚህም ከኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት የንባብ፣ የታሪክና የመረጃ ሀብቶች ጋር በተያያዘ በጋራ ለመስራት ዕቅድ እንዳላቸው አስታውቀዋል።
የቻይና ልዑካኑ ዛሀኦ ዚያንሺ በቻይና የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ቴክኖሎጂ እና የትምህርት መርጃ ልማት ማዕከል ምክትል ዋና ዳይሬክተር፣ ሊ ጂንፔንግ በቻይና የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ቴክኖሎጂ እና የትምህርት መርጃ ልማት ማዕከል የዲቪዥን ዳይሬክተር፣ ሺን ዩን በቻይና የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ቴክኖሎጂ እና የትምህርት መርጃ ልማት ማዕከል የዲቪዥን ዳይሬክተር እና ኪን ዚዩቢንግ የቻይና ኢምባሲ በኢትዮጵያ የባህል ቢሮ ተቀዳሚ ጸሐፊ ናቸው።
ልዑካኑ በኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ጉብኝታቸው በጣም መደሰታቸውንና ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ያስመዘገበቻቸው የጽሑፍ ቅርሶች የተቋሙ አካል ሆነው በማየታቸው አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
በተለይም በጥንታዊ የስነ ጽሑፍ ሀብቶች ላይ በተቋሙ የተሰራው የማሰባሰብ እና የመጠበቅ ስራን የበለጠ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
የልዑካን ቡድኑ ከተቋሙ በጋራ ለመስራት የሚያግዙ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንዲቻል በጉብኝቱ ማብቂያ ላይ ከዋና ዳይሬክተር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አባተ ካሳው እና ከሰነድና መዛግብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ጠና ጋር ውይይት አድርገዋል።