የኃላውን ያላወቀ የወደፊቱን ለማወቅ ይከብደዋል፡፡ የቀ/ ጠ/ፍ/ ቤ/ፕ (ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ)

ግንቦት 14/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ለታላቁ የጥበብ ፈርጥ የበርካታ ግጥምና ዜማዎች ፕሮዲውሰር ያየህይራድ አላምረው እህት ወ/ሮ ሒሩት አላምረው እና ለአቶ ዘላለም አላምረው(ሼፍ ዚ)የምስጋና የምስክር ወረቀት አበረከተ፡፡
የዛሬዎቹ ተመስጋኞቻችን ወ/ሮ ሒሩት አላምረው እና ዘላለም አላምረው (ሼፍ ዚ)በዚሁ ዓመት በታኀሣሥ 22/2018 ዓ.ም የታላቅ ወንድማቸውን የታላቁን የጥበብ ፈርጥ የበርካታ ግጥምና ዜማዎች ፕሮዲውሰር ያየህይራድ አላምረው በሕይወት ዘመኑ ያሰባሰባቸውን ከአምስት ሺህ በላይ መጻሕፍት፣ጋዜጣ፣የጽሑፍ እና የሙዚቃ ኅትመት ውጤቶችን ውድ ስብስቦች ራሱን የቻለ ቦታ በመስጠት የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት በስሙ የተሰየመ የንባብ ክፍል በማዘጋጀት አደራጅቶ ለንባብ ክፍት በማድረግ ለተተኪው ትውልድ የሚጠቅም ታላቅ ስራ መሰራቱ የሚታወስ ነው፡፡
ዛሬ ግንቦት 14/2018 ዓ.ም ወ/ሮ ሒሩት አላምረው እና አቶ ዘላለም አላምረው (ሼፍ ዚ) የታላቁን የጥበብ ፈርጥ የበርካታ ግጥምና ዜማዎች ፕሮዲውሰር ያየህይራድ አላምረው የጽሑፍ ሀብቶች በክብር ተጠብቆ ለአንባቢ ክፍት ወደተደረገበት እና በስሙ ለተሰየመው ቤተመጻሕፍት ለሚያነቡ ተገልጋዮች በቀላሉ የሚጠቀሙበት ግምታቸው ከ1ሚልየን ብር በላይ የፈጁ ሁለት ኮሙፒውተር ለተቋሙ በስጦታ አበርክተዋል፡፡
በእውቅና መርሐ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎትን በመወከል ንግግር ያደረጉት አቶ መኮንን ከፋለ ተቋሙ በርካታ የአገር ሀብትን ጠብቆና ሠንዶ ለትውልድ የሚያስተላልፍ ሀገራዊ  ተቋም በመሆኑ የዛሬ ተመስጋኞች የታላቁ አገር ወዳድ የታላቁ የጥበብ ፈርጥ የበርካታ ግጥምና ዜማዎች ፕሮዲውሰር ያየህይራድ አላምረው ቤተሰቦች ይሄንን ለአገር እና ለትውልድ የሚጠቅም ስራ በመስራታችሁ ተቋማችን ከልብ ያመሰግናችኋል ብለዋል።
የምስጋናና የእውቅና መርሐ ግብሩ ላይ በእንግድነት የተገኙት የቀድሞ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕረዘዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ዛሬ ያየህይራድ በህይወት ባይኖርም ለትውልዱ በማሰብ የሰበሰባቸው ሀብቶቹ የሀገር ሀብት እንዲሆኑ ጠብቆ ያቆያቸውን ቤተሰቦቹ በዚህ መልክ ወደዚህ ሀገራዊ ተቋም ወደሆነው ግዙፍ ተቋም ተጠብቆ ለትውልዱ እንዲያገለግል በማድረጋችሁ ክብር ይገባችኃል። አክለውም ለንባብ ክፍት የተደረገው በወንድማችሁ ስም ለተሰየመው ቤተመጻሕፍት ቤት አንባቢ እንዲጠቀምበት ዘመኑን የማከለ ኮምፒውተር እንደሚያስፈልገው አውቃችሁ ለዚህ አገራዊ ተቋም በወንድማችሁ ስም በማበርከታችሁ ለእናንተም ለወንድማችሁም ትልቅ ደስታን ይሰጣል ብለዋል።የኃላውን ያላወቀ የወደፊቱን ለማወቅ ይከብደዋል።
ወ/ሮ ሒሩት አላምረው ተቋሙ ላደረገላቸው ሁሉ አመስግነው በስጦታ ከተሰጠው ኮምፒውተሮች በተጨማሪ በወንድማቸው  ስም ለተሰየመው ቤተመጻሕፍት አስፈላጊ ናቸው የሚባሉ ቁሳቁሶችን ሁሉ ከሟሟላት ወደኃላም እንደማይሉ ቃል ገብተዋል።
በመጨረሻም ከተቋሙ የተዘጋጀውን የእውቅና የምስክር ወረቀት ለሁለቱም በማበርከት ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡
በእውቅናና የምስጋና መርሐ ግብሩ ላይ የቀድሞ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕረዘዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ፣ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ተወካይ እና የተቋሙ የአብያተ መዛግብትና አብያተ መጻሕፍት ስልጠናና ምክር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መኮንን ከፋለ፣ የተቋሙ የማኔጅመንት አባላት፣ወ/ሮ ሒሩት አላምረው እና አቶ ዘላላም አላምረው እንዲሁም የቅርብ ወዳጆቻቸው ተገኝተዋል።

Share this Post