"የንባብ ባህል ለትምህርት ጥራት!"በሚል መሪ ቃል የሕጻናት የንባብ ሳምንት በሃያት ተካሒዷል።

የማህበረሰብ ዕድገት መሰረቱ እውቀት ነው እውቀት ደግሞ የሚቀሰመው ከንባብ ገጾች ነው።

ግንቦት 8/2018 ዓ.ም አዲስ አበባ

የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት"የንባብ ባህል ለትምህርት ጥራት!"በሚል መሪ ቃል አዲስ ህይወት በሃያት የጋራ መኖሪያ ቤቶች የሕጻናት የንባብ ሳምንት ተካሒዷል።

የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የጋራ መኖሪያ ቤቱ የልማት ኮሚቴው ጸሐፊ ወ/ሮ ጸደይ አለነ የዛሬው እለት ለማኀበረሰባችን ትልቅ ትርጉምና የላቀ እሴት ያለው ታላቅ በመሆኑ ይህን የንባብ ባህል ለማጎልበት፣ሕጻናትና ወጣቶች ከመጽሐፍት ጋር ያላቸውን ትስስር ለማጥበቅ፣እንዲሁም በእውቀት የዳበረ ትውልድ ለመቅረጽ በጋራ በመቆማችን ታላቅ ኩራትና ደስታ ይሰማናል።

"አንባቢ ሕዝብ የበለጸገ ሕዝብ ነው"እንደሚባለው የማህበረሰብ ዕድገት መሰረቱ እውቀት ነው።እውቀት ደግሞ የሚቀሰመው ከንባብ ገጾች ነው።መጽሐፍት የአስተሳሰብ አድማስን ያሰፋሉ፤ የሰውን አርቆ አሳቢነት ያሳድጋሉ፤ሰውን ወደላቀ የሕይወት ምዕራፍ እንደሚመሩ በተለይም ለሕጻናት ንባብ የፈጠራ ችሎታና የአእምሮ ዕድገት መሰረት፣ለወጣቶች ደግሞ ጊዘዜያወቸውን በአዎንታዊና ፍሬያማ በሆነ መንገድ እንዲጠቀሙበት የሚያስችል ታላቅ መሣሪያ እንደሆነ ተናግረዋል።

የተቋሙ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሀገሬ መኮንን በመክፈቻ ንግግራቸው እንደዚህ ዓይነት ኃላፊነት በሚኖርባቸው ጠንካራ አመራሮች ባሉበት ስለሕጻናት የሚያስቡ ለነገ ሀገር ተረካቢ ተተኪ ይሁኑልን የምትሉ እና የምትተሳሰቡ ነዋሪዎች ባላችሁበት ተቋሙ አልፎ አልፎ የሕጻናት የንባብ ሳምንታቶችን እንደሚያዘጋጅ እና ከጥቂቶቹ አንዱ በመሆናችሁ የእናንተ ልጆች እድለኞች ናቸው ብለዋል።

አክለውም ለልጆቻችሁ የምትቆረቆሩ ወላጆች እና በተለይ አመራሮቹ በሕጻናት ላይ መስራት ቀላል አይደለምና ከዚህ በተሻለ ከጠነከሩ ከዚህ ውስጥ ዶክተሮች፣መምህራኖች፣ኢንጅነሮች ወዘተ የሚፈጠሩት ከዚህ መሐል በመሆኑ የተሻለች ኢትዮጵያንና ሀገር ተረካቢ ዜጋን ለመፍጠር የሁላችንንም ርብርብና ተጋግዞ መስራት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

ወጣቶች ላይ የንባብ ክህሎታቸውን ለማምጣት እኛም መላጆች በማንበብ ልምድ ለልጆቻችን ማካፈል እንደሚኖርብንና ቀድመን እኛ ስንለወጥ ልጆችንንም አንባቢ ማድረግ እንችላለን ብለዋል።

ተቋሙ ከዚህ በፊት አዲስ ህይወት በሃያት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ስር ለሚገኘው የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት የተለያዩ ይዘት ያላቸው በበጀት ከ300 ሺህ ብር በላይ የፈጁ 600 መጽሐፍት በስጦታ በማበርከት በአሁን ወቅት በርካታ ተማሪዎች የሚገለገሉበት እንዲሆን እንዳስቻለም ተነግሯል።

በዝግጅቱም የሕጻናት መጽሐፍት ለእይታና ለንባብ ሲበቁ፣የህጻናት ስዕል መሳል፣የአሸንጉሊት ትርኢት፣በኮሜድያን አስረስ በቀለ የተዘጋጀ አስተማሪ አጭር ጭውውት፣ተረት እና ጥያቄ ለሕጻናቱ ቀርቧል።

በመጨረሻም ግጥም ላቀረቡ፣ በንቃት ሲከታተሉን ጥያቄ ሲመልሱ ለነበሩ ሕጻናቶች ከተቋሙ የተዘጋጀ መጽሐፍ በስጦታ ተበርክቶላቸው ከዚህ በፊት በጋራ መኖሪያ ቤቱ ለተደራጀው ቤተመጻሕፍት አጠቃቀም ከባለሙያዎች ሃሳብ በመስጠት የተደራጀውን ቤተመጻሕፍት በተሳታፊዎች ተጎብኝቶ መርሐ ግብሩ ተጠናቋል።

 

Share this Post