ከአንድ ሚሊየን ዘጠና ሺህ ብር በላይ የፈጁ መጽሐፍት በስጦታ ተበረከቱ።
ጥር 26/2018 ዓ.ም በገልማ አባገዳ አዳራሽ
የኢትዮጵያ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ይዘታቸው የትምህርት፣የጠቅላላ እውቀት፣ የሥነ-ጽሑፍ፣የሥነ ልቦና እና የታሪክ የሆኑ በቁጥር 2907 (ሁለት ሺህ ዘጠኝ መቶ ሰባት) በባሌ ዞን ለሚገኙ አስራ አምስት አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቤተ መጻሕፍት እና ለሮቤ ማረሚያ ቤት አበርክቷል።
በዕለቱም የመጻሕፍት ሽያጭና አውደ ርዕዮ ተከፍቶ የንባብ ሳምንት፣ የተማሪዎች የጥያቄና መልስ ውድድር እንዲሁም የፓናል ውይይት መድረክ በሮቤ ከተማ በሚገኘው ገልማ አባገዳ አዳራሽ በርካታ ተሳታፊዎች በተገኙበት ተካሒዷል።
በመርሐ ግበሩ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት የጽ/ቤት ኃላፊ እና የዋና ዳይሬክተሩ ተወካይ አቶ አባተ ካሳው፣የኦሮሚያ ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ጀሚላ ሲቢሮ፣የኦሮሞ ባህል ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ መኪያ ጀማል፣ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ም/ ኃላፊ ዶክተር ቡልቶሳ ኤርኮ፣ የኦሮሚያ የማህበራዊ ክላስተር ዘርፍ ም/አስተባባሪ አቶ ኑራ ጉዮ፣የባሌ ዞን ም/ አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም ኃይሌ፣የሮቤ ከተማ ከንቲባ አቶ ዲኖ አሚን፣የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶ/ር ኑረዲን አማን፣ደራሲ ኢሳያስ ኦርዶፋ እና ደራሲ ይታገሱ ጌትነት፣ሚድያዎች፣የባሌ ዞን የባህል አምባሳደር ቡድንና የማህበረሰቡ ተወላጅ ድምጻዊያን፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ጥሬ
የተደረገላቸው በርካታ እንግዶች ተገኝተውበታል።
በዝግጅቱም ትምህርት አዘል ጭውውቶች በባሌ ዞን የባህል አምባሳደር ቡድን ሲቀርብ በቅርቡ በማህበረሰቡ ቋንቋ ተጽፎ ለህትመት ከበቃው መጽሐፍ በአንድ አመራር ተነቦ ለጥያቄና መልስ ተወዳደሪ ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው መጽሐፉ ተበርክቷል።
የዳበረ ንባብ ባህል ለትምህርት ጥራቱ በሚኖረው አስተዋጽኦ ዙሪያ በመደወላቦ ዩኒቨርሲቲ በተባባሪ ፕሮፌሰር ኦብሳ ማሞ መነሻ ጽሑፍ ለውይይት ቀርቦ ከተሳታፊዎች አሳብ አስተያየት ተሰጥቶበታል።
በጥያቄና መልስ ውድድር ተሳትፈው ከ1-3 ለወጡ አሽናፊ ተማሪዎች የአገልግሎቱ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አባተው ካሳው የመጽሐፍት ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።
በመጨረሻም በኦሮሚያ ባህል ማዕከል የተዘጋጀ የክልሉን የቱሪስት መስህቦች ባህላዊ ፎቶ ምስሎች ለአገልግሎቱ፣ በኦሮሚያ ክልል ስር ለሚገኙ ተቋማቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች ተበርክቶላቸዋል።