የሚኖር ቃል፣የማይጠፋ ቅርስ (የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በአቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት)

ታኀሣሥ 22/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት የታላቁን የጥበብ ፈርጥ የበርካታ ግጥምና ዜማዎች ፕሮዲውሰር ያየህይራድ አላምረው በሕይወት ዘመኑ ያሰባሰባቸውን ከአምስት ሺህ በላይ መጻሕፍት፣ጋዜጣ፣የጽሑፍ እና የሙዚቃ ኅትመት ውጤቶችን ውድ ስብስቦች ራሱን የቻለ ቦታ በመስጠት እና በስሙ የተሰየመ የንባብ ክፍል በማዘጋጀት አደራጅቶ ለንባብ ክፍት አድርጓል፡፡

በመርኀ ግብሩ የዝግጅቱን ዓላማ ያስተላላፉት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት ሁላችን በምናውቀው ታሪኩ፤ ያየህይራድ አላምረው፤ የግጥም እና ዜማ ደራሲ እንዲሁም ፕሮዲውሰር እንዲያም ሲል የታላላቅ ሙዚቃዊ ፕሮጀክቶች ነዳፊ ኢንተርፕረነር ነበር፡፡ ለብዙዎቻችን በሚያስገርም እና በሚያስደንቅ፣ ብዙም ባልተነገረለት፣ ጥቂት የቅርቦቹ በሆኑ ወዳጆቹ እና በቤተሰቦቹ ዘንድ ብቻ በሚታወቅ ልምዱ ደግሞ፤ የንባብ ፍቅሩን ብዙ እጥፍ የሚያስከነዳ መጽሐፍ ሰብሳቢነቱ አስደናቂ ነበር በማለት ምስክርነትን ሰጥተውለታል፡፡

አክለውም ከኅልፈቱ በኋላ የተገለጸው ምሥጢሩ ይህ መጻሕፍትን እጅግ አድርጎ የመውደዱ ነገር ነው ቢባል ማጋነን አይኾንም፡፡ “ምን ሲያደርግ ሰበሰባቸው?” የሚያስብሉ መጻሕፍትን እና ያልታተሙ መዛግብትን መሰብሰቡን የኅልፈቱ ዜና ከተሰማበት ታኅሣሥ 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ቀደም ባሉ ቀናት የወጡ አዳዲስ መጻሕፍትን ሳይቀር ገዝቶ እያነበበ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ እነዚህን መጻሕፍት በወጉ አደራጅቶ የሚያስቀምጥበት ቤት እንደሚያስፈልገው ለቤቶች ኮርፖሬሽን ማመልከቻ እስከመጻፍ ባደረሰ ፍቅር፣ መጻሕፍቱን የሚያስቀምጥበት ክፍል ቢጠበውም እንኳ፣ መጻሕፍትን ከመሰብሰብ ግን አልመቦዘኑንና ለአገሩ ያለውን ፍቅርና ለመጪው ትውልድ አሻራውን ያሳረፈም እንደነበር ተናግረዋል፡፡

በመርኀ ግብሩ በክብር እንግድነት የተገኙት የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳም ስለ ፕሮዲውሰሩ ያየህይራድ ታላቅ የጥበብ ፈርጥ እና ንባብን በቁም ነገር የሚያነብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረ/ፕ ነብዩ ባዬ ያየህይራድ የሰራውን ስራ ለማወቅ የእርሱን ስራ አንብቡ፣ያየን ውብ ለስላሳ ያደረገው እውቀት ያለው ሰው በመሆኑ ነው በማለት አንባቢነቱን መስክረውለታል፡፡

የቅርብ ጓደኛው ድምጻዊ አረጋኸኝ ወራሽም ስለ ያየህይራድ ብዙዎቻችን የሠራናቸውን ሥራዎች እንኳን የመሰብሰብ ልምዱ የለንም ያየ ተቀደው የሚጣሉ ታሪኮች ሳይቀሩ አስቀምጧል፡፡ያየ በጣም ቀና ሰው ነው ለመተቸት ሳይሆን ለማስተካከል የሚሞክር፣በሚሰራቸው ሥራዎች አዳዲስ ቃላቶችን በማምጣት ለሁላችንም የሚረዳ ነው፡፡

ይህንኑ በመመልከት ኮሚቴ በማዋቀር  ከዚህ ዓለም የተለየባት ቀን ለማሰብ ማህበር መመስረቱንም ተናግሯል፡፡

አንጋፋው የሙዚቃ አቀናባሪ ዳዊት ይፍሩም ስለፕሮዲውሰሩ የሰራውን ሥራ ለማሳየት አምጥቶ ሲታይለት እናንተ ያያችሁት ሁሉ ትክክል ነው በማለት የሚቀርብ ልበቀና እና በእውቀቱ ልክ የማይኮራ ታላቅ የእውቀት ሰው ነው ሲል መስክሮለታል፡፡

እህቱ ወ/ሮ ሒሩት አላምረውም ወንድሜ በለፋው፣ በደከመው ልክ ቦታ እንዲያገኝ መንገድ አሳየኝ እያልኩ ፈጣሪዬን ስለው እርሱ ግን እስከመቀመጫው ቦታ እመራሻለሁ ብሎ ፍጻሜውን አሳመረልኝ ስትል ምስክርነቷን፤በተጨማሪም ተቋሙ ለሰጣት እውቅናና ክብር አመስግናለች፡፡

በመርኀ ግብሩ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት፣የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ፣የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ዴኤታ ረ/ፕ ነብዩ ባዬ፣አንጋፋው የሙዚቃ አቀናባሪ ዳዊት ይፍሩ፣የሙያ ባልደረቦቹ እና የዚህ ዓላማ ጠንሳሽ እህቱ ሒሩት አላምረው እና በርካታ ቤተሰቦቹ ተገኝተውበታል፡፡

በመጨረሻም በቀድሞ ስሙ ወመዘክር የአሁኑ የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት በ1936 ዓ.ም ሚያዝያ ወር ሲቋቋም የነበረውንና በያየህይራድ ተጠብቆ የቆየውን መተዳደሪያ ደንብ እህቱ ወ/ሮ ሒሩት አላምረው ለተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ለአቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት እና ለፕ/ር ነብዩ ባዬ አበርክተዋል፡፡

Share this Post