እንኳን ደስ አላችሁ፥እንኳን ደስ አለን!!!

ግራንድ አፍሪካን የተቋማት እና የአመራር ሽልማት ድርጅት፥ ታኅሣሥ 12 ቀን 2018 ዓ.ም. በዓድዋ መታሰቢያ ሚውዚዬም በተዘጋጀ ታላቅ የሽልማት ሥነ ሥርዓት፣ ተቋማችንን (ተቋማችሁን)፥ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት (ወመዘክርን)፥ የወርቅ ደረጃ ተሸላሚ ተቋም አድርጎ ሸልሞታል።

ቤተጻሕፍት ወመዘክር ከተቋቋመበት ከ1936 ዓ.ም. ጀምሮ፣ "ሀገረ መጻሕፍት" የተሰኘችውን ውዲቷ ሀገራችንን፣ መጻሕፍቷን እና መዛግብቷን በዘመናዊ መልክ አሰባስቦ አንባቢ እና ተመራማሪ ትውልድ የመፍጠር፣ ዕውቀት እና መረጃ የሚደራጅበትን ሥርዓት የማበጀት ሥራ እየሠራ 82 ዓመታትን ዘልቋል።

በዚህ ለአንድ ምዕተ ዓመት እየተጠጋ ባለ የተቋም ዕድሜ ውስጥ፥ በሕይወተ ሥጋ የተለዩን እና ከእነሱ ተቋሙን ተረክበው ዛሬም በቅንነት እና በትጋት እያገለገሉ ያሉ ሠራተኞቹ ለዚህ በሕዝብ ፊት ለተሠጠው ታላቅ ዕውቅና ቀዳሚ ተመስጋኞች ናቸው።

ተቋሙን ከ1936 ዓ.ም. ጀምሮ የመሩ 14 አመራሮች፥ ከክቡር አቶ ሠረቀ ብርሃን ገብረ እግዚእ ጀምሮ፣ ክቡር አቶ አርአያ ኃይለ ሥላሴን፣ ክቡር ብላታ ሣሕሌ ጸዳሉን፣ ክቡር አቶ ከበደ ሚካኤልን፣ ክቡር አቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያን....እንዲሁም ክቡር አቶ ይኵኖ አምላክ መዝገቡን፥ የተቋሙን ስም እና ክብር በሚመጥን መልኩ ለሠጡት አመራር እና ላኖሩት ደማቅ አሻራ የተሠጠ ዕውቅና እንደኾነም እናስባለን።

ለተቋሙ ባላቸው ፍቅር የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ትልቅ እገዛ የሚያደርጉ በጎ አድራጊ የተቋሙ ወዳጆችም የተመሰገኑበት ዕውቂያ እና ሽልማትም ነው ማለት ይቻላል።

ከዚህ ኹሉ በላይ፥ የወደፊቱን ሥራችንን በጥንቃቄ፣ በትጋት፣ ዘመንን በሚዋጅ ሥልት እና ዐቅድ የመፈጸም አደራም የሚጥልብን ኾኖ አግኝተነዋል። ስለኾነም፥ ከሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ማግስት ጀምሮ ወገብን አጥብቆ የመሥራት ኃላፊነትን ያስገነዘበን በሕዝብ ፊት የተሠጠ አደራም ጭምር ነው።

ግራንድ አፍሪካን የሽልማት ድርጅትን ለሠጠን ዕውቅና ከልብ እናመሰግናለን። ለተቋማችን ሠራተኞች እና የማኔጅመንት አባላት፣ እንዲሁም ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ የሚለውን መልእክት ሳቀርብ እጅግ ታላቅ ደስታ እየተሰማኝ ነው። የስኬት ባለውለታዎችን ኹሉ ወክዬ በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝቼ፥ ከክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ (የኢፌዴሪ የቀድሞ ፕሬዝዳንት) እጅ ሽልማቱን በመቀበሌ የተሰማኝ ደስታ ወሰን የለውም። ዕውቅናውን ከነአደራው መረከቤን በዚሁ አጋጣሚ መግለጽ እወዳለሁ።

                 እንኳን ደስ አላችሁ፥ እንኳን ደስ አለን።

                     ታኅሣሥ 12 ቀን 2018 ዓ.ም.

                              ሠርፀ ፍሬስብሐት

      የኢትዮጵያ ቤተመዛግብት እና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት

Share this Post