የዓለም የኦዲዮ ቪዥዋል ቅርሶች መታሰቢያ ዕለት በታሪካዊ ሁነት ታጀበ

የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት (ወመዘክር) የዓለም የኦዲዮ ቪዥዋል ቅርሶች መታሰቢያ ዕለትን ጥቅምት 17/2018 ዓ.ም ከዩኔስኮ ጋር በመተባበር በተቋሙ አክብሯል።

ተቋሙ ይህን ልዩ ዕለት በተለየ መልኩ የሚያጎላውን የኢትዮጵያ የጽሑፍ ቅርሶች አስመዝጋቢ ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን ይፋ ያደረገበትም ሆኗል።

በዚህ መርሐግብር የተከበሩ ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር፣ክቡር ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ የባህልና ስፓርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እና የኢትዮጵያ የጽሑፍ ቅርሶች አስመዝጋቢ ብሔራዊ ኮሚቴ የክብር አባል፣ዶ/ር ሪታ ቢሶኖት የዩኔስኮ በአዲስአበባ ዳይሬክተር፣ፕሮፌሰር አሉላ ፓንክረስት፣ ኤምሬትስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ፣ የኃይማኖት እና የማህበረሰብ ጥናትና ምርምር ተቋማት እንዲሁም ታላላቅ የታሪክና የምርምር አጥኚዎች በተገኙበት የኢትዮጵያ የጽሑፍ ቅርሶች አስመዝጋቢ ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋም ይፋተደርጓል።

ኮሚቴው በህዳር ወር 2025 ሁለት ጥንታዊያን የሀገራችንን ታላላቅ የጽሑፍ ቅርሶች በዓለም የትዝታ (የትውስታ) ማኅደር ለማስመዝገብ አስፈላጊውን ሰነድ የማሟላት ስራ ሲሰራ መቆየቱንና ከዚህ በኋላም በየሁለት አመቱ በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ጥንታዊያን የጽሑፍ ቅርሶችን የማስመዝገብ ስራን እንደሚያከናውን የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰርፀ ፍሬ ስብሐት አሳውቀዋል።

የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ከዛሬ 20 አመት በፊት 12 ያህል የጽሑፍ ቅርሶችን በዓለም አቀፍ የሰው ልጆች የአእምሮ ሀብትነት የማስመዝገብ ስራ መስራቱ ይታወሳል።

Share this Post