በደቡብ አሪ ወረዳ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች የመጽሐፍት ስጦታ ተበረከተ::
የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ት/ት ቢሮ እና ወርልድ ቪዥን በአዘጋጅነት የተሳተፉበት "የንባብ ባህል ለት/ት ጥራት!" በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው የንባብ ሳምንት የሚመለከታቸው የመንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎችና ታዳምያን በተገኙበት በደቡብ አሪ ወረዳ ሸጲ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተካሔዷል።
የዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ክቡር አቶ አብረሃም አታ የትምህርት ግብዓቶች እጥረት በመንግስት ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ የሁሉንም አካላት ትብብር የሚፈልግ ነው በማለት በጥምረት ስለተዘጋጀው ሁነት አመስግነዋል።
የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ፕረዝዳንትና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ክቡር አቶ አበረ አዳሙ ባስተላለፉት መልዕክት እውቀት እርቦናል በንባብ እንጥገብ፤ በኢትዮጵያ ሁሉም በአንድ አብሮ የሚነሳበት የንባብ አብዮት ያስፈልገናል በሚሉ ሀሳቦች ላይ ገለፃ አድርገዋል።
ዝግጅቱ የተማሪዎች የጥያቄና መልስ ውድድር እና የሽልማት መርሀ ግብር አካቷል።
የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት በደቡብ አሪ ወረዳ ለሚገኙ ሁለት አንደኛ፣ ሁለት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደዚሁም ለጂንካ የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት በስጦታ ያበረከተውን 368,482 ብር ያወጡ 1,205 መጻሕፍት የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት ለደቡብ አሪ ወረዳ ት/ት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ካሳሁን አሰግድ እና ለደቡብ አሪ ዞን ባህል ቱሪዝም ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ጠልክስ አስረክበዋል።