"የንባብ ባህል ለትምህርት ጥራት!" በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው የንባብ ሳምንት ተካሔደ።

የቀድሞ የሕጻናት አምባ ምሥረታ 45ተኛ ዓመትን ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ከአላጌ ግብርና ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ጋር በመተባበር የተዘጋጀው የንባብ ሳምንት፣ስልጠና እና የፖናል ውይይት መድረክ ከነሐሴ 24/2017 ዓ.ም ጀምሮ በልዩ ድምቀት ተካሒዷል። በዝግጅቱ የተቋሙ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አባተ ካሳው እና የሚመለከታቸው ባለሙያዎችና ሥራ አስፈጻሚዎች፣የአላጌ ግብርና ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ዲን ረዳት ፕሮፌሰር መርክነህ መሰኔ፣ደራሲ ይታገሱ ጌትነት እና ደራሲ ገዛኸኝ ሀብቴ፣ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መ/ር ዶ/ር ተሻገር ሽፈራው እንዲሁም የአላጌ ጊዜያዊ ቁስለኞች ማገገሚያ አዛዠ ኮሎኔል ምስባሁ አረብ እና በማገገሚያ ማዕከሉ የሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት ተገኝተዋል። በመርሐ ግብሩ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በኮሎኔል ምስባሁ አረቡ በኮሌጁ ዲን ረዳት ፕሮፌሰር መርክነህ መስኔ የመክፈቻ ንግግር ተደርጓል። በተቋሙ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አባተ ካሳው የመርሐ ግብሩን ዓላማ አንባቢ ትውልድን ለማፍራት የእኛ ተቋም አጠናክሮ እንደሚሰራ ተናግረው መረጃን አደራጅቶ በመያዝ ዛሬ ወደእናንተ ሲመጣ ስለእናንተ የተሰነዱ መዛግብትን ይዞ በምልከታቹ በዘመኑ የነበሩ ትዝታዎችን ወደኃላ ሄዳችሁ የምትመለከቱበትም ትልቅ አጋጣሚ መድረክም እንደሆነ ተናግረው ግምታቸው ከሦሥት መቶ አርባ አራት ሺህ ብር በላይ የፈጁ አንድ ሺህ መጽመፍት ይዘታቸው የትምህርት መርጃ እንዲሁም የታሪክና የፍልስፍና የሆኑ መጻሕፍት በስጦታ መበርከቱን ጠቁመዋል። በመድረኩም አነቃቂ ንግግሮች እና የህይወት ተሞክሮዎች በታላላቅ ሰዎች ሲቀርቡ የጥያቄና መልስ ውድድርና በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረቱ የሥነ ጽሑፍ ስራዎች መልዕክት አዘል ግጥሞችም ቀርበዋል። የንባብ ባህል ለትምህርት ዘርፍ ስላለው አስተዋጽኦ በመ/ር ዶ/ር ተሻገር ሽፈራው፣ በአስር አለቃ ሳለ አማረ እውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተጻፈ "የተሰበረው ንስር" መጽሐፍ በጸሐፊው ቀርቧል። በቤተ መጻሕፍት ሙያ እና በሰነድና መዛግብት አስተዳደር ስልጠና ወስደው ላጠናቀቁ ሰልጣኞች የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ያዘጋጀውን የምስክር ወረቀት እንዲሁም የሥነ-ጽሑፍና የጥያቄና መልስ ተወዳዳሪዎች የመጽሐፍት ስጦታ ከተቋሙ ሥልጠና እና ማማከር ሥራ አስፈጻሚ አቶ መኮንን ከፍ ያለ እጅ ተበርክቶላቸዋል። በበጀት ከሦሥት መቶ አርባ አራት ሺህ ብር በላይ የፈጁ በይዘታቸው የትምህርት መርጃ እና ታሪክና ፍልስፍና የሆኑ በቁጥር አንድ ሺህ መጽሐፍ ለአላጌ ግብርና ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ፣ለሻላ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት፣ለዘራይ ድረስ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት እንዲሁም የቁስለኞች ማገገሚያ ማዕከል ለኮሌጁ ዲን ረ/ ፕ መርክነህ እና ለጊዜያዊ ማገገሚያው አዛዠ ኮሎኔል ምስባሁ የተቋሙ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አባተ ካሳው በስጦታ አበርክተዋል። በዛው መድረክ ላይም ከዛጎል መጽሐፍ ባንክ በቁጥር ሁለት መቶ መጽሐፍት፣ ከኢትዮጵያን ሪድስ ስድስት መቶ በአማርኛና በኦሮምኛ ቋንቋ የተጻፉ የልጆች መጽሐፍት እና ከአምባ ልጆች የተሰባሰቡ በርካታ መጽሐፍት ተበርክተው የመጀመሪያው ቀን መርሐ ግብር ተጠናቋል።

Share this Post