የኢትዮጵያ ቤተመዛግብት እና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት የሚጠቀምበትን አዳራሽ መድረክ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ሠርቶ ለማስረከብ የሚረዳ የጋራ ስምምነት ተፈረመ

የአዳራሽ መድረኩን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለማደስ ስምምነቱ የተፈረመው በኢትዮጵያ ቤተመዛግብት እና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት እና በአቶ አምኃ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ መካከል ሲሆን ስምምነቱንም የአገልግሎቱ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አባተ ካሳው እና የብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ልጅ አቶ አምኃ መርስዔ ኀዘን መጋቢት 15/2017 ዓ.ም ተፈራርመዋል፡፡

የተቋሙ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አባተ ካሳው ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ የዛሬው የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ይጠራበት የነበረው “ወመዘክር” የሚለውን ስያሜ ከመስጠት ጀምሮ አሰባስበው የያዟቸውን መዛግብት ለተቋሙ በመስጠት እንዲሁም በሀገራችን ጥንታውያን መዛግብትና መጻሕፍት ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ ጭምር ያደረጓቸው አስተዋጽኦዎች እጅግ በርካታ እንደሆኑ የጋራ መግባቢያ ስምምነቱን ሲፈራረሙ ተናግረዋል፡፡

በመግባቢያ ስምምነቱ ላይ የተገኙት ልጃቸው አቶ አምኃ መርስዔ ኀዘን ይህን የአባታቸውን ፈለግ በማስቀጠል ተቋሙን በተለያየ ጊዜያት ሲደግፉ እንደቆዩና አባታቸው ሲጠቀሙባቸው የነበሩ ታሪካዊ መዛግብት እና መጻሕፍትን ለተቋሙ በተለያየ ጊዜ ማበርከታቸውን ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ በዝግጅቱ የተገኙት የአብያተ መዛግብትና የአብያተ መጻሕፍት ስልጠናና ምክር ስራ አስፈጻሚ አቶ መኮንን ከፋለም በኢትዮጵያ ቤተመዛግብት እና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት የሚገኙት የብላታ መርስዔ ኀዘን የመዛግብት ስብስቦች ተቋሙ ካሉት የግለሰብ መዛግብት ስብስቦች መካከል ተመራማሪዎች በስፋት የሚጠቀሟቸው መዛግብት እንደሆኑም ምስክርነታቸውን ሰጥተው በማከልም ልጃቸው የአባታቸውን አርአያ በማስቀጠል እስከ ዛሬ ለሌሎችም አርአያ በመሆናቸው ተቋሙ እውቅና እንዲሰጣቸው ጠቁመው የመግባቢያ ስምምነቱን የተቋሙ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አባተ ካሳው እና የብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ  ልጅ አቶ አምኃ መርስዔ ኀዘን ተፈራርመው ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡

Share this Post