በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በጀሙ ከተማ የንባብ ሳምንትና አውደ ውይይት መድረክ ተከፈተ::
የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ባህል፣ ቱሪዝምና ስፓርት ቢሮ ጋር በመተባበር ከመጋቢት 1/2017 ዓ.ም ጀምሮ “ማንበብ በጥበብ ጎልብቶ ለማበብ!” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው የንባብ ሳምንት እና አውደ ውይይት መድረክ በጀሙ ከተማ መካሄድ ጀምሯል::
በመርሀግብሩ ላይ የእንኳን ደና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የምዕራብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ክቡር አቶ ጌታቸው ኪኔ እኔ የማውቀውን አዳራሽ ውድ በሆነውና በማያልቀው የአዕምሮ ሀብት በመጻህፍት ስጦታ አሸብርቃችሁ ስለጠበቃችሁን ደስ ብሎናል ብለዋል::
በመቀጠል ንግግር ያደረጉት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት የትምህርት ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ማርቆስ ቡልቻ ከሩቅ እስከ ቦታው ድረስ ደርሳችሁ ውድ ስጦታ በመስጠታችሁ ትውልድ የማይረሳውን አሻራ አሳርፍችኋል ብለዋል::
የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አባተ ካሳው በበኩላቸው የክልሉን አስተዳደር ተጋባዥ ደራስያንና ታዳምያንን አመስግነው ይህ መርሀ ግብር ተሰንደው ያሉ ዕውቀቶችን ለህዝቡ ተደራሽ ከምናደርግባቸው መንገዶች አንዱ መሆኑን ገልጸዋል::
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ተወካይ አቶ አስማማው ምህረት በንግግራቸው ከዚህ ቀደም በሌሎች የክልሉ ከተሞች የተከናወኑትን የንባብ ሳምንታት አስታውሰው ተቋሙ ንባብን ባህሉ ያደረገ ትውልድን ለማፍራት እየሰራ ላለው ስራ አመስግነዋል::
በመርሀግብሩ ላይ የምዕራብ ኦሞ ዞን የባህል ክነት ቡድን በአከባቢው ማህበረሰብ ባህላዊ ውዝዋዜ ታዳሚያንን አዝናንተዋል::