ለሀገር ጥቅም የሚሰጡ ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈረመ፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ከአማራ ህዝብ ዝክረ-ታሪክ ማዕከል ጋር ጥር 27/2017 ዓ.ም የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል፡፡

በመግባቢያ ሰነዱ ላይ የተቋሙ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አባተ ካሳው ባስተላለፉት መልዕክት የአማራ ክልል ሰነዶችን አደራጅቶ ከመያዝ አንጻር በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተቋሙ በርካታ ስራዎችን በሰራበት ወቅት የተመለከቱትን መልካም ተሞክሮዎች ተናግረው ክልሉ ጥሩ የሀገር ሀብት ያለው በመሆኑ ተጋግዘን በመስራት ለሀገር የሚጠቅመውን እናስቀድማለን ብለዋል፡፡

እንደተቋምም በሚፈለጉ የሙያ ስራዎች ባለሙያዎችን በመላክ ስልጠናዎች እንደሚሰጡና የአቅም ማጎልበት ስራ እንደሚሰራ ጠቁመው አካባቢው በብዙ ውጣውረዶች ውስጥ ያለፈ በመሆኑ ገፅታን የመቀየሩ ስራ ተጠናክሮ መሰራት እንዳለበትም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

የአማራ ህዝብ ዝክረ ታሪክ ማዕከል የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አዲስ በየነ በበኩላቸው ወደዚህ ተቋም እድሉ ተፈጥሮ በመምጣታቸው አመስግነው የክልሉ ህዝብ በሀገረ መንግስት ግንባታው ላይ የነበረውን ሚና የሚገልጹ ታሪካዊ መረጃዎችንና ጥናትና ምርምሮችን ደረጃውን በጠበቀ ቤተ-መጻሕፍት እና ቤተ-መዛግብት መሰነድና ማደራጀት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

እነዚህንም የጽሑፍ ቅርሶች አመዘጋገብና አያያዝ በሚመለከት የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ይህን ተግባር በአዋጅ ተሰጥቶት የሚያከናውን ተቋም በመሆኑ በማዕከሉ የታቀዱ ተግባራትንም ለማከናወን እንዲሁም የልምድ ልውውጥ ለማድረግም ሆነ የግብዓት ድጋፍ ለማግኘት በጋራ መስራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም የመግባቢያ ሰነዱን የተቋሙ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አባተ ካሳው እና የአማራ ዝክረ ማዕከል ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አዲስ በየነ ተፈራርመው ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡

Share this Post