የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ስለተሰጠው መጻሕፍት ስጦታ አመሰገነ፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት  በዓለም ታሪክ ላይ የሚያጠነጥኑ 825 መጻሕፍት ከተባባሪ ፕሮፌሰር ዴቪድ ቻፕል  በስጦታ መልክ ተረክቧል፡፡ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዴቪድ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ የትምህርት ዘርፍ ውስጥ ከ 50 ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎትም በመኖርያ ቤታቸው በመገኘት በቀን 15/05/2016 ዓ.ም ተቋሙን በወከሉት የአብያተ መጻሕፍት መረጃ ሀበቶች ማሰባሰብ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ስለሺ ሽፈራው አማካኝነት የምስጋና የምስክር ወረቀት አበርክቷል፡፡

ተባባሪ ፕሮፌሰር ዴቪድ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1936 በእንግሊዝ ሀገር ውስጥ ተወልደዋል፡፡ ከፍተኛ ትምህርታቸውንም በካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ በሲድኒ ሰሴክስ ኮሌጅ የሚሰጠውን የትምህርት ዕድል ተወዳድረው በማሸነፍ በታሪክና ስነ-መለኮት ትምህርት ከ1957-1960 እ.ኤ.አ ተከታትለዋል፡፡

በ1968 እ.ኤ.አ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ሲሆን በSandford English School በመምህርነት እስከ 1971 እ.ኤ.አ አገልግለዋል፡፡ በመቀጠልም የአ.አ ዩኒቨርሲቲን የታሪክ ትምህት ዘርፍ ተቀላቅለው በረዳት ፕሮፌሰርነት እንዲሁም በተባባሪ ፕሮፌሰርነት የዓይን እይታቸውን እስካጡበት 2022 እ.ኤ.አ ድረስ በዓለም ታሪክ መምህርነት እና የዲግሪ፣ የማስተርስ እንዲሁም የዶክትሬት መመረቂያ ጽሁፎችን በማማከር ቆይተዋል፡፡ የለገሷቸው መጽሀፍትም አለም አቀፋዊ የታሪክ እውቀታቸውን ጥልቀት ነፀብራቅ ሆኖ የሚወሰድ ነው፡፡

Share this Post