የሰንደቅ ዓላማ ቀን ተከበረ፡፡
የሰንደቅ ዓላማ ቀን ተከበረ፡፡
በአገራችን ኢትዮጵያ ለአስራ ስድስተኛ /16ኛ/ ጊዜ “የሰንደቅ አላማችን ከፍታ ለህብረ ብሔራዊ አንድነታችንና ሉአላዊነታችን ዋስትና ነው!” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ የሚገኘውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት፣ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እና ከብሔራዊ ቲያትር ጋር ጥቅምት 5/2016 ዓ.ም በደማቅ ስነ ስርዓት አክብሯል፡፡
በክብረ በዓሉ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ክቡር አቶ ቀጄላ መርዳሳ፣የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ክብርት ወርቅነሽ ብሩ፣የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት አመራሮችና ሰራተኞች እንዲሁም የብሔራዊ ቲያትር አመራሮችና ሰራተኞች ተገኝተዋል።
በበዓሉም የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የተከበሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳ የመክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ በንግግራቸውም የባንዲራ አከባበር በኢትዮጵያ ብዙም ያልተለመደ እና ከዛሬ አስራ ስድስት ዓመት በፊት ማክበር እንደተጀመረ፤ አከባበሩም ስላልተለመደ በሕግ ተወስኖ እንደተጀመረ ጠቁመው የባንዲራን ምንነት በብዙው ማህበረሰብ ዘንድ የሚታወቅና ባንዲራም ሰፊ ታሪክ እንዳለውና በዓለም ላይና በዓለም ዙሪያ ገና ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ ሰዎች ባንዲራን ለተለያዩ ጉዳዮች ምልክትነት ሲጠቀሙ እንደነበር መታወቁንም ሲጠቁሙ በተለይም በጦር ሜዳ፤በባህር ላይ ጉዞ በመርከቦቻቸው ላይ እንደሚጠቀሙበትና በኃላ ግን በ18ኛው ክፍለ ዘመን መንግስታት እንደ ብሔራዊ መንግስታት መቋቋም እንደተጀመረና ብሔርተኝነት አድጎ ብሔራዊ መንግስታት መቋቋም ሲጀምሩ ብሔራዊ ባንዲራ ወደ ህዝባዊነት ሲቀየር የወታደር ምልክት መሆኑ ቀርቶ የአገርና የህዝብ ምልክት ሆኖ ማገልገል እንደጀመረ ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥም በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ አካባቢዎች ህዝቦች ምልክቶች ነበሯቸው እንደ ባንዲራ የሚጠቀሙበት ምልክቶች እንደነበሯቸው በኃላ ግን ዘመናዊ ኢትዮጵያ ስትመሰረት አንድ ባንዲራ በአገር በአጠቃላይ እንደአገር ስንጠቀምበትና ሲጠቀሙበት እንደነበር እንደሚታወስና ባንዲራ በየጊዜው በታሪክ አጋጣሚ እንደሚሻሻልና ሊቀየርም እንደሚችል፤ ሰዎች ተስማምተው፣አገር ተስማምቶ የሚያደርጉት የሚቀየረው ደግሞ ታሪካዊ አጋጣሚ ሲኖር እንደሆነ፤ መንግስታት ይቀያየራሉ ነገስታት የሚጠቀሙበት ባንዲራና ዲሞክራሳዊ የሆነ ሕዝብ ወይም ሀገር የሚጠቀሙበት ባንዲራ እንደሚለያይ እና በዲሞክራሲያዊ ሀገር ንቃተ ሕሊና ስላለ ሕገ መንግስታዊ ስርዓት ያላቸው ሀገሮችና ዲሞክራሲያዊ ሕገ መንግስት ያላቸው ሀገሮች ባንዲራቸውን በጋራ ተስማምተው እንደሚወስኑም ተናግረዋል፡፡
አክለውም ዛሬ ያለው የሀገራችን ሰንደቅ ዓላማ በሕገ መንግስቱ ተደንግጎ የተቀመጠና የቀለማት ቅርፅና ትርጉም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት ያለውን ስያሜን በተመለከተ ሲገልጹም አረንጓዴው የኢትዮጵያ እድገትና ልምላሜን እንደሚወክል፤ቢጫው ተስፋ፣ፍትህና እኩልነትን እንደሚወክልና ቀዩ የህዝብ ነፃነት እኩልነት፣መስዋትነትንና ጀግንነትን ሲወክል ኮከቡ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በእኩልነት ላይ የተመሰረተውን አንድነት ማሳያ እንደሆነ እና ክብ የሆነው ሰማያዊ መደብ ሠላምን የሚገልጽ እንደሆነም መልዕክት አስተላልፈው ሠንደቅ ዓላማው በክቡር ሚኒስተሩ ተሰቅሎ የዕለቱ መርሐ ግብር ተጠናቋል፡፡