የንባብ ቀን በማረሚያ ቤት ተካሔደ

መጻሕፍት ለዕውቀት ገበታ፣መዛግብትና የጽሑፍ ቅርሶች ለታሪክ ትውስታ በሚል መሪ ቃል የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ከደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር መጋቢት 2/2015 ዓ.ም በተጀመረው የመጀመሪያው ዙር የመዛግብትና የጽሑፍ ቅርሶች ጉባዔ በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ከአለቃ ተክሌ ገ/ሀና አዳራሽ በተጨማሪ በደብረ ታቦር ከተማ ማረሚያ ቤት መጋቢት 3/2015 ዓ.ም በተነቃቃና በደመቀ መልኩ የንባብ ቀን ተካሒዷል።

በዝግጅቱም የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር አነጋግረኝ ጋሻው፣የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ም/ኘሬዘዳንት ዶ/መንበሩ ተሾመ፣የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ፣የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ቱሪዝምና ኪነ ጥበባት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሒሩት ካሳው፣የደቡብ ጎንደር ማረሚያ ቤቶች መምሪያ ኃላፊ ኮ/ር ዋለልኝ አሻግሬና የማረሚያ ቤቱ የማኔጅመንት አባላት የሐይማኖት አባቶች፣መምህር አገኘሁ አዳነ፣ደራሲ በሁሉም አለበል፣ታራሚዎችና  ከአገልግሎቱ አመራሮችና ሰራተኞች ተሳትፈዋል።

በዕለቱም የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ጎንደር ማረሚያ ቤቶች ኃላፊ ኮ/ር ዋለልኝ አሻግሬ የመጽሐፍት ልሳን የንባብ ክበባት በማረሚያ ቤት ማቋቋም ዜጎች በፈፀሙት ወንጀል ተፀፅተው አውቀውና ተምረው ለነገ አስተማሪና መካሪ ዜጋ ሆነው እንዲወጡ በተቋሙ ውስጥ የንባብ ጊዜ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የእውቀት ባለቤት ይሆኑ ዘንድ ወሳኝ በመሆኑ ይህ በጎ እና የሰዎችን አመለካከት የሚቀይር ተግባር መሰራቱ እንዳስደሰታቸውና የዚህ በጎ ተግባር ጠንሳሾቹንና ሁለቱን አዘጋጆቹን ተቋማት አመስግነዋል።

የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር አነጋግረኝ ጋሻው በማረሚያ ቤት ንባብ ምንም የሚጎዳ ሳይሆን የሚጠቅም በመሆኑ ባህል በማድረግ በውጩ ኑሯችን ያላዳበርነውን ተሞክሮ እድሉን ለመልካም ነገር በመጠቀም መለወጥ እንደሚቻልና ይህ የዛሬ መልዕክት ለታራሚዎች ብቻ ሳይሆን ሁሉም ቦታው ላይ ለተገኘ ተሳታፊ ራሳችንንና ቤተሰባችንን የምንቀይርበት ጊዜ ነው በማለት መልዕክታቸውን ሲያስተላልፉ ዶ/ር ሒሩት ካሳውም ይህ ዛሬ ያለንበት ስፍራ በመጀመሪያ ስሙ ተቀይሮ ከእስር ቤት ወደ ማረሚያ ቤት መቀየሩ ስሙ እራሱ አስተማሪ ነው።ማረሚያ ቤት ስያሜው ትምህርት ቤት ማለት ነው።በእኛ እድሜ ት/ት የሚሰጥበት ሆኖ ማግኘታችን ደስተኛ እንዳደረጋቸውና ማረሚያ ቤቶች ከቀለም ትምህርቱ በተጨማሪ የተለያዩ የእደ ጥበብ ምርቶች የሚሰሩበት በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸው ታራሚው እንደ በጎ ተሞክሮ ወስዶ መጠሚያ ሊያደርገው እንደሚገባ መክረው አክለውም በማረሚያ ቤቶች አሁን እየተሰራ ያለውንና የዚህ በጎ ተግባር ጠንሳሽ የሆኑትን የአገልግሎቱን ዋና ዳይሬክተር አመስግነው የዚህ ዓይነቱ ተግባር  ባህርዳር ማረሚያ ቤት ከዚህ ቀደም መካሔዱን አስታውሰው ጥናት ሲደረግ አንድ ታራሚ በዓመት 50 መጽሐፍትን እንዳነበቡና በማንበብ ህይወታቸውን እንደቀየሩም ተናግረዋል።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡም ዝግጅቱን በተመለከተ ታራሚዎች ወደማህበረሰቡ በሚቀላቀሉበት ወቅት አንብበው ብቁ ዜጋ እንድትሆኑ ለማስቻለ ነው።

ታራሚዎች ባነበቡት መጽሐፍ ልክ የእስር ቀናታቸው እንደሚቀንስ በሌሎች ያደጉ አገራት ያለ ተሞክሮ እንዳለና ይህንንም ተሞክሮ ወደ ሀገራችን ለማምጣት ከሚመለከታው አካል ጋር እየተነጋገሩ እንደሚገኙና ተግባራዊ እስከሚሆን ድረስ ተግተው እያነበቡ እንዲጠብቁ ተናግረዋል።

በዕለቱም በማረሚያ ቤት ውስጥ ያለውን ዓለም በምናብ መኖር በመምህር አገኘሁ አዳነ እና በደራሲ በሁሉም አለበል ንባብና ባህርይ በሚል ርዕስ የንባብ ህይወት ልምዳቸውን ተሞክሮ ለታራሚው ሲቀርብ ጥያቄዎችን ለመለሱና ስነ ጽሑፍ ላቀረቡ ታራሚዎች የተለያዩ የእውቀት ዘርፍ ያላቸው መጽሐፍት ተበርክቶላቸዋል።

በመጨረሻም  ለደብረ ታቦር ከተማ ማረሚያ ቤት ከአገልግሎቱ የተበረከቱ  በብር አንድ መቶ ሃያ አምስት ሺህ የፈጁ በቁጥር 502 መጽሐፍት የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት  ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖ አምላክ መዝገቡ ለደቡብ ጎንደር ማረሚያ ቤቶች ኃላፊ ኮ/ር ዋለልኝ አሻግሬ አበርክተዋል።

 

Share this Post