በወላይታ ሶዶ ከተማ የመጻሕፍት ስጦታ እና የንባብ ክበባት ምስረታ መርሐግብር ተከናወነ
የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ከደቡብ ህዝቦች ብሔር ብሔረሰቦች ክልላዊ መንግስት ባህል ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር በወላይታ ሶዶ ከተማ የካቲት 13 ቀን 2015 ዓ.ም በህዝብ ቤተ መጽሐፍት በነበረው የንባብ ክበባት ምስረታ መድረክ ላይ ለአራት አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች፣ ለአራት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ለእያንዳንዳቸው 200 መጽሐፍት በገንዘብ ሲተመን 252,828 ብር እና ለወላይታ ሶዶ የህዝብ ቤተ መጽሐፍት 1000 መጽሐፍት በገንዘብ ሲተመን 240,541 ብር እንዲሁም ለቦዲቲ የ2ተኛ ደረጃ ት/ቤት 200 መጽሐፍት በገንዘብ ሲተመን 43,531 ብር እና ለቦዲቲ የህዝብ ቤተ መጽሐፍት 1000 መጽሐፍት በገንዘብ ሲተመን 28,991ብር ያበረከተ ሲሆን የእንኳን ደህና መጣችሁ እና የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ ክቡር አቶ ተመስገን አለማየሁ ከየኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት የአብያተ መጽሐፍት አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ተፈራ ተረክበዋል።
በመርሐግብሩ ላይ ደራሲ ዘነበ ወላ፣ ደራሲና ሀያሲ ገዛኸኝ ሀብቴ እና ደራሲ ሊዲያ ተስፋዬ ከንባብ ክበባት አመሠራረት፣አስፈላጊነት እና ጠቀሜታን በሚመለከት ከስምንት ት/ቤቶች ለተውጣጡ የአንደኛ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እና መምህራን የንባብ ልምድና ተሞክሮዎችን በመጨመር ገለፃ እና ውይይት አድርገዋል።
በአሳታፊ ጥያቄዎች ለተሳተፉ እንዲሁም ግጥም ላቀረቡ ተማሪዎች የመጽሐፍት ስጦታ የተበረከተ ሲሆን የዞኑ የባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሾመ ሀብቴ የማጠቃለያ ንግግር አድርገዋል።