የንባብ ሳምንትና አውደ ውይይት ተካሔደ

የኢትዮጽያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ከምስራቅ ጎጃም ዞን ባህልና ስፖርት መምሪያ ጋር በመተባበር "ለንባብ ወደ ቤተ-መጻሕፍት እንሩጥ! "በሚል መሪ ቃል የንባብ ሳምንትና አውደ ውይይት ጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም አካሄደ።

በዝግጅቱም የምስራቅ ጎጃም ዞን ባህል፣ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ተወካይ ወ/ሮ ውብዓለም ልዑል፣የሞጣ ከተማ ከንቲባ ተወካይ አቶ አለልኝ አለኸኝ፣የሞጣ ከተማ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፀሐይ ወንድሙ፣ መምህር መሰረት አበጀና ደራሲ ይፍቱስራ ምትኩ፣የኢትዮጽያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ያሬድ ተፈራ እና የሚመለከታቸው የስራ ክፍል ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም የተጋበዙ የሞጣ ከተማ ነዋሪዎች ፣ መምህራንና ተማሪዎች ተገኝተዋል።

በዝግጅቱም የሞጣ ከተማ ሰባቱ ዋርካ ባህል ኪነት ቡድን ባህላዊ ጭፈራ በማቅረብ ታዳሚውን ሲያዝናኑ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በሞጣ ከተማ ከንቲባ ተወካይ በአቶ አለልኝ አለኸኝ ሲደረግ በመልክታቸውም አሁን በሀገራችን እየታየ ያለውን የትምህርት ስብራት በዘንድሮ ተማሪዎች ውጤት እንደታየ ጠቁመው ለዚህ የትምህርት ስርዓታችን ማንሰራራት እና ብቁ ዜጋ ለመፍጠር በመጽሐፍት የተደራጀ ቤተ መጻሕፍት አስፈላጊ በመሆኑ ወመዘክር ለሞጣ ከተማ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ቤቱ ከለገሰው በርካታ መጽሐፍት በተጨማሪ በዘርፉ እውቀት ያላቸውን ባለሙያዎች ያላንዳች ክፍያ ሞጣ ድረስ በመላክ ከተለያዩ ተቋማት ለተውጣጡ 23 የቤተ መጻሕፍት ባለሙያዎች ስልጠና መስጠቱን ተቋሙን አመስግነው ስልጠናውን ያገኙ ሰልጣኞችም ስልጠናውን በተግባር እንዲያውሉ ሲናገሩ የምስራቅ ጎጃም ዞን ባህል፣ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ተወካይ ወ/ሮ ውብዓለም ልዑልም እንደ ከንቲባው የተሰጡ ስልጠናዎች ተሰልጥነው ብቻ የሚቀሩ መሆን እንደሌለባቸውና አንድን ሀገርና ትውልዱን ለመቀየር ትምህርት ላይ ጠንክሮ መስራት እንደሚጠበቅ ተናግረው አገልግሎቱ ንባብን አስመልክቶ ቀድሞ በክልሎችና ከተሞች እየሰራ የሚገኘው ጠንካራ እና ትውልድ የማይረሳው የሚበረታታና ለለውጥ የሚታትር መሆኑን የሚያመላክት እንደሆነም ተናግረዋል። ከተወካይዋ በመቀጠል መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ተወካይ አቶ ያሬድ ተፈራ ተቋሙ የተሰጠውን ተልዕኮ ለማስፈጸም ዛሬ በቤተ መጻሕፍት ሙያ ዘርፍ የበቁ ባለሙያዎች እንዳይፈልቁ ትምህርቱ በዩኒቨርሲቲዎች እንደ ሀገር እየተሰጠ ባይሆንም የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ይህንኑ ክፍተት ለመሸፈን በሙያው የሰለጠኑና እውቀቱ ያላቸውን አሰልጣኞች ድጋፉን ለሚፈልጉ ክልሎች እና ከተሞች ዘርፉ ላይ ተመድበው የሚያገለግሉ ባለሙያዎች ሙያውን አግኝተው እንዲሰሩ በማሰልጠንና በማደራጀት እንዲሁም መጽሐፍትን በመለገስ አንባቢ ትውልድ እንጂ ጠብ ጫሪና ሀገር አፍራሽ ትውልድ እንዳይሆን እየሰራ የሚገኝ ተቋም እንደሆነም ጠቁመው አክለውም ተቋሙ ዛሬ ወደ ሞጣ ከተማ የመጣው ቤተ መጻሕፍቱን በማጠናከር እና በዘርፉ ባለሙያዎች ተደራጅቶ የተጎበኘው ቤተ መጻሕፍት ቀጣይነት ኖሮት አገልግሎት መስጠቱ ሳይቋረጥ ተደራጅተው የተቀመጡት መጽሐፍት እየጠፉም እየተቀደዱም እንዲነበቡ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሆነም ተናግረዋል።

 

Share this Post