የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት በዱራሜ ከተማ የንባብ እና አውደ ውይይት መርሐግብር እያከናወነ ነው

የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ከደቡብ ህዝቦች ብሔር ብሔረሰቦች ክልላዊ መንግስት ባህል ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር በዱራሜ ከተማ ያዘጋጀው የንባብ እና አውደ ውይይት መርሐግብር  የካቲት 10 ቀን 2015 ዓ.ም የጀመረ ሲሆን በዚሁ ዕለት በተደረገው በአብያተ መዛግብትና አብያተ መጽሐፍት አንኳር ጉዳዮች ላይ የተዘጋጀውን አውደ ውይይት የከተማው ከንቲባ አቶ ዘመዴ ሄራሞ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር፣ የዞኑ ዋና አስተዳደር ልዩ አማካሪ  አቶ ዘማች ጢሞቲዎስ የመክፈቻ ንግግር እንዲሁም የደቡብ ህዝቦች ብሔር ብሔረሰቦች ክልላዊ መንግስት ባህል ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ አቡቶ አኒቶ ስለ መርሐግብሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዚህ መርሐግብር በዘርፉ ላይ የሚሰሩ የተቋሙ ከፍተኛ ባለሙያዎች አቶ አባተ ካሳው " የዛሬ ሰነዶች የነገ መዛግብት በጥበቃና እንክብካቤ ዙሪያ የባለድርሻ አካላት ሚና" በሚል ርዕስ፣ አቶ አብይ ሐይሉ " የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ክምችት በወፍ በረር" በሚል ርዕስ፣ ወ/ት ገነት ተስፋዬ " የመረጃ ሀብቶች ስታንዳርድ" በሚል ርዕስ፣ ወ/ት ፌቨን አሸናፊ "የመረጃ ሀብቶች ጥበቃና እንክብካቤ" በሚል ርዕስ የመወያያ ጽሑፍ አቅርበው በተሳታፊዎች ውይይት የተደረገበት ሲሆን ከመዛግብት እና ከመረጃ ሀብቶች ጋር በተገናኘ ያሉ ችግሮች፣ መፍትሔዎች እና ፋይዳቸው ላይ ሰፊ የሀሳብ ልውውጥ ተደርጓል።
ይህ መርሐግብር የከምባታ ጠምባሮ ዞን የባህል ቡድን ክልሉንና አካባቢውን የሚያስተዋውቁ ልዩ የኪነጥበብ ስራዎችን አቅርቦ አድናቆት ያገኘበትም ነው።

Share this Post