ተቋሙ ያደራጀውን ቤተ-መጻሕፍት አስመረቀ

የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶችና ህፃናት ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ስር በሚተዳደረው የአካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ልማት ማዕከል ቤተ-መጻሕፍት አደራጅቶ አስመርቋል፡፡

በዝግጅቱም የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አባተ ካሳው በንግግራቸው ተቋሙ ንባብን ለማስፋፋት በመላው ሀገሪቱ የሚያደርገውን ጥረት ጠቅሰው በዚህም ማዕከል የምትገኙ የጦር ጉዳተኞች ለእኛ ጀግኖቻችን በመሆናችሁ እናንተን ማገልገል በመቻላችን እድለኞች ነን ሲሉ ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶችና ህፃናት ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ገነት ቅጣው ስለተደረገው ትብብር አመስግነው የማዕከሉ አባላት መጻሕፍቱን ከማንበብም ባለፈ ታሪካቸውን ሰንደው ለትውልድ ማስተላለፍ እንዲችሉ አበረታተዋል፡፡

ንባብን በማስመልከት የህይወት ተሞክሯቸውን ያካፈሉት ደራሲ ሊዲያ ተስፋዬ እና ደራሲ ይታገሱ ጌትነት  ለሀገር ባለውለታ የሆኑ ታዳምያን የህይወት ተሞክሮ ተሰንዶ እና ለህትመት  በቅቶ ተተኪው ትውልድ ታሪካቸውን የሚዘክረው መሆን እንደሚገባውና ማየት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም ተቋሙ ያደራጀውን  በማዕከሉ ቅጥር ጊቢ የሚገኘውን ቤተ-መጻሕፍት የተቋሙ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አባተ ካሳው፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶችና ህፃናት ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ገነት ቅጣው እና ከጦር ጉዳተኞች ማህበር ተወካይ በጋራ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገው ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡

Share this Post