አብያተ መጻሕፍት በዲጂታል ዘመን መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች ላይ ተሞክሮችን የሚያካፍሉ የፓናል ውይይት መድረክ ተካሔደ

የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት፤ ሚዛን አማን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ፣የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ባህል ቱሪዝምና ስፓርት ቢሮ ፤ ቤንች ሸኮ ባ/ቱ/ስፓርት መምሪያ እንዲሁም ሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር በመተባበር ከታሕሣሥ 15-18/2015 ዓ.ም. ባካሄደው የንባብ ሳምንት፣ ቡክፌር፣ የመጻሕፍት አውደ ርዕይና የፓናል ውይይት መድረክ እና ኤግዚቢሽን አካል የሆነው  አብያተ መጻሕፍት በዲጂታል ዘመን መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች በሚል ርዕስ በሚዛን አማን በሚገኘው ሳላይሽ ሆቴል ይፓናል ውይይት ተካሒዷል።

በፓናል ውይይቱ ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ፣ ከተለያዩ ተቋማትና ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ የቤተ መጻሕፍት ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል።

በዝግጅቱ ላይ የሚዛን ቴፒ ፕሬዘዳንት ዶ/ር አህመድ ሙስጠፋ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክ/መ/ባ/ቱ/ስ ቢሮ ተወካይ አቶ ወንድሙ ለማ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም በአሁን ዘመን ወጣቱ ከማንበብ ይልቅ የተለያዩ ማህበራዊ ሚድያዎች ላይ ግዚያቸውን በሚያሳልፉበት ወቅት የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ለንባብ ትኩረት ሰጥቶ ወደ እኛ መጥቷል እኛም  የጣላችሁብንን አደራ ለመወጣት ከእኛ የሚጠበቀውን ተግተን እንድንሰራ አድርጋችሁናል ብለዋል። ለዚህም አክብሮትና ምስጋናቸውን ለተቋሙና ሰራተኞቹ ሰጥተዋል።

በመርሐ ግብሩ ከአገልግሎቱ በወ/ሪት ገነት ተስፋዬ የመረጃ ሀብቶች ማሰባሰብና ደረጃውን የጠበቀ አዘገጃጀት ለማህበረሰብ ተደራሽነት ያለው ጠቀሜታ፣በአቶ አዲስ ብርሃኔ ዲጅታል ቤተ መጻሕፍት ያለው መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች፣በወ/ሮ ኤልሳቤት አሸናፊ ዲጅታል ቤተ መጻሕፍት ከብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አንጻር የመነሻ ጽሑፎች እና ተሞክሮዎች ለውይይት ሲቀርቡ ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በረዳት ፕሮፌሰር ጥላሁን በቀለ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የድጅታል ቤተ መጻሕፍት ተሞክሮ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።

በመጨረሻም ከተሳታፊዎች እንደ ሀገር የላይብረሪ ሳይንስ ሙያ ድሮ ዩኒቨርስቲዎች ላይ ይሰጥ ነበር ነገር ግን አሁን ያ የትምህርት ዘርፍ ተቋርጧል ይሔ የሚቀጥልበትና እኛም ሙያችንን ለማሳደግ እንፈልጋለን ይሔ እንዴት ይመቻቻል? ብዙ ግዜ ካታሎግ ስንሰራ የሀገር ውስጥ መጽሐፍቶች ካታሎግ የላቸውም የውጮቹ መጽሐፍት እንጁ?  ደረጃን ከማስጠበቅ አንጻር ኃላፊነቱ የማነው? ስታንደርድ ባለመኖሩ የሚመጣ ጉዳት አለ ወይ? በየግል የቀረቡት ጽሑፎች ጥሩ ናቸው ነገር ግን ሰዓቱ አንሷል ምናልባት ስልጠና ቦታው ድረስ መጥተን እንኳን መሰልጠን ባንችል በኦንላይን ብታመቻቹልን የሚሉ  አሳብ አስተያየት እንዲሁም ጥያቄዎች ተነስተው የሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ሲሰጡ የእለቱ የፓናል ውይይቱ አወያይ የነበሩት አቶ ያሬድ ተፈራ ለተነሱ ጥያቄዎች ጥቅል ምላሽ ሰጥተው የፓናል ውይይቱ ተጠናቋል።

Share this Post