በሚዛን አማን ከተማ ሲካሔድ የነበረው የንባብ ሳምንት ፣ ቡክፌር፣ የመጻሕፍት አውደ ርዕይና ኤግዚቢሽን ተጠናቀቀ

መጻሕፍት ለእውቀት ገበታ፤መዛግብትና የጽሑፍ ቅርሶች ለዘመን ትውስታ! በሚል መሪ ቃል ለአራት ተከታታይ ቀናት በሚዛን አማን ከተማ ሲካሔድ የነበረው የንባብ ሳምንት ፣ ቡክፌር፣የመጻሕፍት አውደ ርዕይና ኤግዚቢሽን ተጠናቋል::  
ዝግጅቱን የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት፣የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጽያ ክልላዊ መንግስት ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ፣ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ፣ የቤንች ሸኮ ዞን አስተዳደር እና የሚዛን አማን ከተማ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፓርት መምሪያ በመተባበር ከታህሣሥ 15-18/2015 ዓ.ማ አዘጋጅተውታል።
በዝግጅቱም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጸጋዬ ማሞ፣ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚ ጉዳዮች ኃላፊ እጬ ዶ/ር ካሳሁን ሙላት፣የሚዛን አማን ከተማ ከንቲባ አቶ ግሩም ተማም፣የደቡብ ምዕራብ ኢ/ያ ክ/መ/ባ/ቱ/ስፓርት ቢሮ ኃላፊ ተወካይ አቶ ወንድሙ ለማ፣ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ፣አንጋፋና ጀማሪ ደራሲያንና ጥሪ የተደረገላቸው መምህራንና ተማሪዎች፣የሚመለከታቸው የአገልግሎቱ ባለሙያዎች እንዲሁም የአካባቢው ማሕበረሰብ ተገኝተውበታል።
በዞኑ የባህል ቡድን ባህላዊ ጭፈራ ደምቆ የተጀመረው ዝግጅት በተከናወኑት ሁነቶች የሚመለከታቸው የመንግስት ተጠሪዎች ዝግጅቱን የሚገልጹ መልዕክቶችን ያስተላለፉበት መርሐ ግብርም ነበር። 
የዝግጅቱ የመክፈቻው ቀንም የዝግጅቱን ዓላማ የያዙ መልዕክቶች በሚዛን አማን ከተማ ከንቲባ በአቶ ግሩም ተማም፣ በሚዛን አማን የዞኑ አስተዳደር ተወካይ በአቶ ሽመልስ መኩሪያ፣በሚዛን አማን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚ ጉዳዮች ኃላፊ በእጩ ዶ/ር ካሳሁን ሙላት፣በክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ በአቶ ጸጋዬ ማሞ፣በክልሉ ባ/ቱ/ስፓርት ቢሮ ተወካይ በአቶ ወንድሙ ለማ፣በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር አህመድ ሙስጠፋ እና በኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር  በአቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ የንባብ አስፈላጊነትና ንባብ ለአንድ ሀገር እድገትም ሆነ ስልጣኔ መሰረት መሆኑን ያደጉ ሀገሮችን ምሳሌ በመስጠት መልዕክቶች ተላልፈዋል።
የመጽሐፍት ስጦታውንም በተመለከተ የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ ለተሳታፊው ሲገልጹ ሚዛን አማን ከተማ ለሚገኙ ለአምስት 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቤተ መጻሕፍት፣ለአምስት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቤተ መጻሕፍት፣ ለአንድ የህዝብ ቤተ መጻሕፍት ቤት፣ለአንድ የወጣት ማዕከል እንዲሁም ለሚዛን አማን ማረሚያ ቤት በአጠጠቃላይ በቁጥር /4230/አራት ሺህ ሁለት መቶ ሰላሳ መጽሐፍት እና በብር 946,684/ ዘጠኝ መቶ አርባ ስድስት ሺህ ስድስት መቶ ሰማኒያ አራት ብር የፈጅ መጻሕፍት ከላይ በዝርዝር ለተጠቀሱት ተቋማት በመረጃ ተይዘው በስጦታ ተበርክተዋል።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር በርክብክቡ ወቅት እነዚህ በስጦታ ለሚዛን አማን ከተማ ለሚገኙ ተቋማት የተበረከቱ መጽሐፍትን የአብያተ መጻሕፍት ኃላፊዎችና ርዕሳነ መምህራን ቤተ መጻሕፍቱን መዝጋት ሳይሆን ተማሪዎች እንዲያነቡበት /አገልግሎት/ እንዲሰጡ እንጂ ተዘግተው እንዳናገኛቸውና መጻሕፍቱም ተማሪዎቹ ተጠቅመውባቸው የቆሸሹ እንጂ አዲስ ሆነው እንዳናገኛቸው በማለት አሳስበዋል።
መርሐ ግብሩም በተማሪዎች የጥያቄና መልስ ውድድር፣በሚዛን አማን ማረሚያ ቤት ለታራሚዎች በተዘጋጀ የንባብ ቀን፣ የወጣቶች የኪነ ጥበብ መድረክ እንዲሁም የንባብ ክበባት ምስረታና የንባብ ባህል ዝግጅቶች ላይ አንጋፋው ደራሲ ፋሲል መንግስቱ፣ ደራሲ ገዛኸኝ ሀብቴ፣ ደራሲ ሊድያ ተስፋዬ፣መምህር መሰረት አበጀ፣ በትምህርት ቤቶች የንባብ ክበብ ምስረታና የንባብ ባህል ላይ ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዋለልኝ ደባልቄ እና መምህርት ሊድያ ተካ እንዲሁም በማረሚያ ቤት የቀድሞው ታራሚ እጩ ዶክተር መምህር አማረ ፈንታሁ ንባብን በተመለከተ የህይወት ተሞክሯቸውን አካፍለዋል።
በቀናቶቹም በኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት የተዘጋጀው ክልሉን ሊገልጹ የሚችሉ ከመዛግብት ክምችት የተወሰዱ መዛግብቶች እና ፎቶግራፎች ፣የጽሑፍ ቅርሶች እና የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ኤግዚቢሽን ለእይታ ክፍት ተደርገው ሲጎበኙ እና ለሽያጭ የቀረቡ የመጽሐፍት ሻጪዎች መጽሐፍት በተማሪዎችና በወላጆች ሲሸጡ ሰንብተዋል።
በመጨረሻም የፖናል ውይይት በተቋሙ የዘርፉ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ሁለት ከሚዛን አማን ዩኒቨርሲቲ በተጋበዙ መምህራን ዘርፎቹን የሚገልጹ የመነሻ ጽሑፎች በአብይ ርዕሰ የአብያተ መጻሕፍት በድጅታል ዘመን መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች ላይ ተሞክሮች እና መዛግብት የትናንት ፣የዛሬና የነገ አገናኝ ድልድይ በሚል  ርዕሰ የተዘጋጁ በርካታ የመነሻ ጽሑፎች ለውይይት ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸው በሚዛን አማን ከተማ ሲካሔድ የነበረው መርሐ ግብር የበበቃ የቡና እርሻ ልማት ተጎብኝቶ ዝግጅቱ ታሕሣሥ 18/2015 ዓ.ም ፍጻሜውን አግኝቷል።

Share this Post