ፍኖተ ንባብ በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው የንባብ ክበብ ምስረታና የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ተከፈተ

ፍኖተ ንባብ በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው የንባብ ክበብ ምስረታና የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ተከፈተ።
የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ከቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት በጋራ ያዘጋጀውን የንባብ ክበብ ምስረታና የመጻሕፍት አውደ ርዕይ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት አርብ 16/2015 ዓ.ም ከቀኑ 8፡00 ሰዓት በቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት አከናውኗል።
በዝግጅቱም የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ፣የቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት ፕሬዘዳንት ወንድም ዳንኤል ካርሊን፣መምህር መሰረት አበጀ እና ሰዓሊ አገኘሁ አዳነ፣የቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት የየዘርፉ ባለሙያዎችና ዳይሬክቶሬቶች፣መምህራን፣ወላጆችና ተማሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተሳትፈዋል።
ዝግጅቱም በትምህርት ቤቱ ፕሬዘዳንት በወንድም ዳንኤል ካርሊን የጸሎት መርሐ ግብር  ከተካሔደ በኃላ በተማሪዎችና በእለቱ የዝግጅቱ ተሳታፊዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር ተዘምሯል። 
እናንብብ የሚለው የአገልግሎቱ መለያ የሆነው ንባብ ላይ ያተኮረ መልዕክት አዘል መዝሙር በአማረ የህጻናት ዝማሬ ታጅቦ ለታዳሚው ሲቀርብ
በዕለቱም የቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት ፕሬዘዳንት የእለቱ መልዕክት እና ተቋሙንና ስራው እንዲ በስኬት እንዲታይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰራ ያደረጉትን የአገልግሎቱን ዋና ዳይሬክተር እና በስራው ላይ የተሰማሩትን አመስግነዋል።
በመቀጠልም በኢትዮጵያ ቤተ- መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በአቶ  ይኩኖአምላክ መዝገቡ ንባብ ላይ ያተኮረ ጥልቅ ንግግር ሲደረግ ዛሬ ተቋማችን በእንደዚህ ዓይነት አንጋፋ ትምህርት ቤት ተገኝቶ የንባብ ክበብን ለመመስረት ሳይሆን ለማነቃቃትም እንደሆነ ተናግረዋል።
ከአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር መልዕክት በመቀጠል ከትምህርት ቤቱ የተዘጋጁ በርካታ የምስጋና የምስክር ወረቀቶች ስራው ላይ ለተሳተፉ ወላጆችና ሰራተኞች ሲበረከቱ ለኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎትም የምስጋና የምስክር ወረቀት እና አዋርድ ተበርክቷል።
በእለቱም በአዲስ መልክ ለተደራጀው የ1ኛ ደረጃ ተማሪዎች ቤተ መጻሕፍት 
ይዘታቸው  ፍልስፍና፣ታሪክ፣ልብወለድና ከ1-12 ክፍል አጋዥ መጻሕፍት የሆኑ በቁጥር 2053 (ሁለት ሺህ አምስት ሦሥት መጻሕፍት) በብር 400,000 ( አራት መቶ ሺህ)የፈጁ መጻሕፍት በስጦታ ተበርክቶ የተደራጅው ቤተ መጻሕፍትም በሐይማኖታዊ ስርዓት ተመርቆ ለተጠቃሚ ተማሪዎች ክፍት ተደርጓል።
በዕለቱም በትምህርት ቤቶች የንባብ ክበብ መመስረት አስፈላጊነት ላይ በመምህር መሰረት አበጀ የግንዛቤ ማስጨበጥ፣የማነቃቃትና የህይወት ልምድ ተሞክሮ ለታዳሚው ሲቀርብ በሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መካከልም የጥያቄና መልስ ውድድር፤አዝናኝና አስተማሪ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችና የተማሪዎች የጥናትና ምርምር ስራዎች ለእይታም ቀርበዋል።
በመጨረሻም የመጻሕፍት አውደ ርዕዩና ከኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ለእይታ የቀረቡ መዛግብቶች እና ፎቶ ግራፎች ለእይታ ክፍት ሲደረጉ ለሶስት ቀናት የሚቆየው የንባብ ክበብ ምስረታና የመጻሕፍት አውደ ርዕይ የሕዳር 16/2015 ዓ.ም የመክፍቻ ሥነ-ሥርዓቱ በተሳካ መልኩ ተጠናቋል።

Share this Post