ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ አድዋ የተሰኘ ልዩ ኤግዚቢሽን ተከፈተ
ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ አድዋ የተሰኘ ልዩ ኤግዚቢሽን ተከፈተ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት /ወመዘክር/ አድዋን መሰረት በማድረግ ያዘጋጀው አድዋ የተሰኘ ኤግዚቢሽን በተቋሙ ግቢ ማክሰኞ ህዳር 13/2015 ዓ.ም ተከፍቷል።
ኤግዚብሽኑን የአሜሪካን ኢምባሲ፣በአሜሪካን መንግስት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች አካል በሆኑት ኮሚኒቲ ኮንሰርትዩም፣ ሄርቴጅ ኮንዘርቬሽን አሶሴሽን፣ ማንዴላ ዋሽንግተን ፌሎሺፕ፣ አይሬክስ በአጋርነት አዘጋጅተዋል።
ከአዘጋጆቹ አንዱ የሆነው ሄርቴጅ ኮንዘርቬሽን አሶሴሽን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሪት ሔዋን ጎይቶም ይህ ኤግዚቢሽን አድዋን ከድሉ በስተጀርባ ያለውን የህብረት፣ ጥረትና አጠቃላይ ሁነት በማሳየት የሚያጎላ እና ጎብኚዎች፣ የታሪክ ምሁራንና ተመራማሪዎች የሚሰጡትን ሐሳብ በማካተት ከ 3 ወር በኋላ በኦን ላይን የሚቀርብ እንደሆነም ገልጸው
በተጨማሪም የታሪክ አጥኚዎች እና ተመራማሪዎች በጉዳዩ ላይ የውይይት መነሻ ጽሑፍ የሚያቀርቡበት የፖናል ውይይት መድረክ ቅዳሜ ህዳር 17 / 2015 ዓ.ም ፍላጎቱ ያላቸው ተሳታፊዎች በሙሉ እንዲገኙ ጥሪ ተደርጎ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ባለሙያ የሆኑት እና የመርሐ ግብሩ አስተባባሪ አቶ ኢሳያስ በላይ በበኩላቸው ይህ ሐሳብ ሲቀርብ በጣም መደሰታቸውንና ተቋሙ ያለውን የጉዳዩን ፎቶ ስብስቦች ከ6 ኪሎ የኢትዮጵያ ጥናት ኢንሰቲትዩት ስብስቦች ጋር በማቀናጀት የጽሑፍ መግለጫውን መዘጋጀታቸውን ገልጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ባሉት ሀገራዊ ሰነዶችና መዛግብቶች የነፃነት አርማ የሆነውን አድዋን በልዩ መልኩ በማሳየት በተለያዩ መነሻዎች ሀገራችን የገጠማትን ፈተና ከልዩነታችን ይልቅ አንድነታችን እንደሚበዛ ማሳየት የሚችልበት ኤግዚቢሽን ነው ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም በልዩ ዲዛይን እና ጥራት ከመዘጋጀቱ በተጨማሪ በየካቲት ወር ለሚከበረው የአድዋ ድል በዓል በደመቀ መልኩ ለማዘጋጀት ቅድመ ዝግጅት ከመሆን ባለፈ የአድዋ ድል ኢትዮጵያ በአለም ሀገራት የሚኖራትን ቦታና የድሉን ዋጋ ከፍ ለማድረግ የካቲት ወርን ሳይጠብቁ ለማውሳት ያለመ መሆኑ ኤግዚቢሽኑን ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
ኤግዚቢሽኑ ከሕዳር 13- 17 /2015 ዓ.ም ያለምንም ክፍያ ለህዝብ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ተጠቁሞዋል።