የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት የሰሜን ዕዝን መታሰቢያ መርሐ ግብር አከናወነ

የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ለጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም አጥቢያ በኢፌድሪ መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ አባላት ላይ በህወሀት በክህደት ጥቃት መፈጸሙን ለማሰብ “ጥቅምት 24ን መቼም አንረሳውም!!” በሚል መሪ ቃል በመላው ሀገሪቱ የሚደረገውን የመታሰቢያ መርሐ ግብር ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እና የሚኒስቴሩ ተጠሪ ተቋማት ጋር ሐሙስ ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አከናውኗል፡፡

በመርሐ ግብሩም መጀመሪያ ላይ የጧፍ ማብራት ስነ ስርዓት ከህሊና ፀሎት እና ታዳሚው "ለኢትዮጵያ የከፈላችሁትን መቼም አንረሳውም" በሚለው መርህ የቀኝ እጁን በደረቱ በማድረግ ለመከላከያ ሰራዊቱ ያለውን ፍቅር ገልጿል።

የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ ቀጀላ መርዳሳ  እንዲሁም ክቡር አምባሳደር መስፍን ቸርነት እና ክብርት ነፊዛ አልመህዲ የዳቦ መቁረስ ስነ ስርዓት ፈፅመዋል።

የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ ቀጀላ መርዳሳ ዕለቱን አስመልክቶ  " ይህ ቀን የሀዘን ቀን ነው። ይሄ ጭፍጨፋ እነ ግራዚያኒ በአዲስ አበባ ከፈፀሙት ጭፍጨፋ ጋር የሚመሳሰል ነው። በሌላ መልኩ ደግሞ ሰራዊቱ ያንን ጥቃት አልፎ ቁመናውን አጠናክሮና አደራጅቶ የመልሶ ማጥቃት በማድረግ በመስዋትነት ሀገራችንን የታደገበት ነው። እናም ሁለት የተደበላለቀ ስሜት በአንድ የሚስተናገድበት ነው።" በማለት የገለፁ ሲሆን ከክቡር አምባሳደር መስፍን ቸርነት እና ከክብርት ነፊዛ አልመህዲ ጋር በመሆን ጉዳዩን የተመለከተ የመወያያ ሰነድ በማቅረብ በታዳሚው ውይይት ተደርጎበታል።

በመጨረሻም ለመከላከያ ሰራዊት በሞባይል የጽሑፍ መልዕክት 6800 አማካኝነት ድጋፍ ተደርጓል።

Share this Post