ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጠ

የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ከንባብ ለህይወት ኢትዮጵያ ፐሮጀክት ጋር በመቀናጀት በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ከሐምሌ 28 እስከ ነሐሴ 02/2014 ዓ.ም. ለሚካሔደው የመጻሕፍትና የትምህርት ተቋማት ኤግዚቢሽን ሐምሌ 25/2014 ዓ.ም. ከጠዋቱ 5፡00 ሰዓት ላይ በኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ በአዘጋጆቹ ተወካዮች ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥተዋል፡፡

ይህንን ተግባር የጀመሩትን በማመስገን ጅማሮውን ያደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ የዘንድሮው የመጻሕፍትና የትምህርት ተቋማት ኤግዚቢሽን የሚካሔደው የንባብ ሳምንት እና አውደ ርዕይ ለተከታታይ አምስት ቀናት እንደሚቆይ ተገልጾ በዝግጅቱም ንባብና ንባብን ሊያጎሉ የሚችል ክዋኔዎች እንደሚከወኑበት ተጠቁሟል፡፡

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖ አምላክ መዝገቡ በጋዜጣዊ መግለቻው ላይ ለመጠቆም እንደሞከሩት ይህንን የንባብ ሳምንትና አውደ ርዕይ ደማቅ ለማድረግ እንዲሁም የከተማውን ነዋሪ የሚመጥን ዝግጅት እዲሆን እንደ ተቋም አጽንኦት በመስጠት እየተሰራ እንደሚገኝና ለዚህ ተግባር ማስፈጸሚያ ተቋሙ ከ 2,600,000 /ከሁለት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሺ ብር/ በላይ በጀት በመመደብ ለመስራት እንደተዘጋጀም ጠቁመዋል፡፡

ተቋምሙ በዝግጅቱ ላይ በዋናነት የፎቶግራፍ እና መዛግብት አውደ ርዕይ፣ የህጻናት ንባብ አገልግሎት እና ለትምህርት ቤቶች የመጻሕፍት ስጦታ እንደሚበረከት ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

Share this Post