የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በተቋሙ ጉብኝትና የስራ ትውውቅ አደረጉ
በዚህ መርሐግብር የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰርፀ ፍሬ ስብሐት ከስራ አመራር አባላት ጋር በመሆን የእንኳን ደህና መጡ አቀባበል እና የሶስት ወራት (የሩብ አመት) የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ማቅረብን አከናውነዋል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰርፀ ፍሬ ስብሐት የተቋሙን አዲሱን ስያሜና አደረጃጀትን ከሀገራዊ የመደመር ጉዞና የተቋሙ ምዕራፎች ጋር በማሰናሰን ተቋማዊ መሠረትን፣ ተቋማዊ ማንነትን፣የሩብ አመቱን አፈጻጸምን፣ ዋና ዋና ውጤቶችን፣ በመደመር ታላቅ ስትራቴጂ የተገኘ እቅድን እና የሚኒስትሩ ትኩረት አቅጣጫን አብይ ጉዳይ በማድረግ ገለጻ አቅርበዋል።
በቀረበው የሩብ አመት አፈጻጸም ለ 2,656,138(ሁለት ሚሊየን ስድስት መቶ ሀምሳ ስድስት ሺህ አንድ መቶ ሰላሳ ስምንት) ዜጎች በቤተ መዛግብት እና በቤተ መጻሕፍት ንባብ፣ ስልጠና፣ ምክር አገልግሎት መሰጠት መቻሉን እና ከእነዚህም 50%(ሀምሳ በመቶ) ሴቶች መሆናቸው ተጠቅሷል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ኪነጥበብና ብራንዲንግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ረ/ፕ ነብዩ ባዬ በበኩላቸው ተቋሙ የሚሰራውን ስራ ቀደም ብለው የሚያውቁት እንደመሆናቸው አሁንም በባለስልጣን አደረጃጀቱ ተቀበል፣አድስ፣አሻግር መርህን መነሻ በማድረግ ያቀደው የጉዞ ምዕራፎች ስኬታማ እንዲሆን እንደ ሚኒስቴር መስሪያቤት እና የበላይ ኃላፊ ብሎም እንደ ዜጋ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ለዋና ዳይሬክተሩ እና የስራ አመራር አባላት አሳውቀዋል።
ተቋሙ በአዋጅ 1440/2019 መሠረት ስያሜው ከአገልግሎት ወደ ባለስልጣን መቀየሩ እንዲሁም ክቡር ረ/ፕ ነብዩ ባዬ የመንግሥት ምስረታን ተከትሎ በሚኒስቴር መስሪያቤቱ የባህል ኪነጥበብና ብራንዲንግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው መሾማቸው የሚታወስ ነው።