የህጻናት ማቆያ መመሪያ አደረጃጀትና አገልግሎት አሰጣጥ የግንዛቤ ስልጠና ተሠጠ።

በስልጠናው ተገኝተው ስልጠናውን የከፈቱት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብት እና ቤተመጻሕፍት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት በተቋማት ደረጃ የህጻናት ማቆያ እና መንከባከቢያ ማዕከላት መኖር የሰው ሀብት ልማትን፣ምቹ የስራ አካባቢን ለመፍጠር፣ለህጻናት ተገቢውን
እንክብካቤ ለመሥጠት ጉልህ  ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
ስልጠናው በተቋሙ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ አመቻችነት
በሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር በአካቶ ትግበራ ሥራ አሥፈጻሚ የተቋማት ማብቃት ባለሙያ በአቶ እንየው ታምሩ ሲሰጥ በስልጠናው የሚመለከታቸው ሥራ አስፈጻሚዎች፣ ሞግዚቶች እና በማቆያው ተጠቃሚ የሆኑ ወላጆች የተሳተፉበት ነበር።
በስልጠናው ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሞከረው የህጻናት ማቆያና መንከባከቢያ ማዕከላት አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ፤ በውስጡ የህጻናት ማቆያ ማዕከላት በተቋማት አካባቢ መኖራቸው ለህጻናት፣ለሴቶች ፣ለተቋም እና ለሀገር ስላለው ጠቀሜታ እና የህጻናት ማቆያ ምንነት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
ባለሙያው አያይዘውም በኢትዮጵያ የሕፃናት ማቆያ አገልግሎት አሰጣጥ በዋናነት በፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 እና በወጣው የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሕፃናት ማቆያ አሠራር መመሪያ ቁጥር 47/2013 እንደሚመራው በአዋጆቹም ዙሪያ ግንዛቤ አስጨብጠዋል።
ስልጠናውን ያመቻቸው የተቋሙ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አገሬ መኮንን ተቋሙ ለአዋጁ ትኩረት በመስጠት  የተቋሙ ሰራተኞች ህጻናት ልጆቻቸውን በወላጆቻቸው አቅራቢያ በመሆን እንክብካቤና ክትትል እንዲደረግላቸው የተመቻቸው ማቆያ ጥሩ ጅማሮ እንደሆነ ገልጸው ነገር ግን ሞግዚቶችና የሚመለከታቸው የሥራ ክፍል የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ የተዘጋጀ ስልጠና እንደሆነ ጠቁመው በስልጠናው የተገኘን ግንዛቤ በመውሰድ የሚቀሩ ነገሮች ተሟልተው ደህንነታቸውና ጤንነታቸው የተጠበቁ ህጻናትን ማቆያው እንደሚያፈራ ተናግረዋል።
በሚድያ(ቴሌቪዥን) ላይ የሚተላለፉ ሱስ የሚያሲዙ እና የተዛቡ ማስታወቂያዎች ህጻናቱን ለተለያየ በሽታ የሚያጋልጡ ጤነኛ ያልሆኑ ምግቦች/ ጣፋጭ እና ለስላሳ መጠጦች፤ከዲጅታላይዝድ አንጻር ለህጻናቱ የማይጠቅሙ ይዘት ያላቸው ባህል እና ቋንቋቸውን የሚያበላሹ ፊልም፣ሙዚቃ ተንቀሳቃሽ ምስሎች የሚያስተዋውቁ ማስታወቂያዎች ሲሰራጩ ትውልዱን ከመታደግ አንጻር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ጠንክሮ በመስራት ማስቆም እንዳለበት ሰልጣኞቹ ጠቁመዋል።
በማጠቃለያው ለሁለት ሞግዚቶች በነበራቸው የስራ ቆይታ ስለነበራቸው ተነሳሽነት የማበረታቻ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።

Share this Post