ከተቋሙ ስብስቦች

የዛሬው የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት በ1936 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ተመርቆ በተከፈትበት ወቅት የሕዝብ ቤተመጻሕፍት ወመዘክር የሚል ስያሜን በመያዝ ንጉሱ ባበረከቱት መጻሕፍት አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ይነገርለታል፡፡ታዲያ ይኸው ተቋም በየዘመናቱ በሚሰጡት መጠሪያ ስሙ የተቋቋመበትን ዓላማ እና ተልዕኮ ለማሳካት እየሰራ ቢገኝም ከ2014 ጀምሮ አሁን የሚጠራበትን የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት የሚለውን መጠሪያ ስያሜውን በመያዝ በቤተመዛግብቱም ሆነ በቤተመጻሕፍቱ ዘርፍ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡

ተቋሙ ሀገራዊ ተቋምነቱን ሊያስመሰክሩ የሚችሉ በውስጡ በርካታ መጻሕፍት፣መጽሔቶች፣ጋዜጦችን እና መጣጥፎች፣ቀረጸ ድምጾችና ምስሎች፣ማኑስክሪፕቶችን፣የነገስታት ደብዳቤዎችን፣ማስታወሻዎች፣ፎቶ ግራፎች፣ካርታዎች፣የተለያዩ የብር ኖቶች፣የጠረፍ ስምምነቶች፣ቆየት ያሉ የፍርድ ቤት መዝገቦች፣ካሴቶችና ሸክላዎች፣በግዕዝ ቋንቋ የተጻፉ የነገስታት ደብዳቤዎችን በማደራጀት ጠብቆ ለትውልድ ለማሻገር የሚሰራ ተቋም ሲሆን በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ጥንታውያን መጻሕፍት እና የነገስታት ደብዳቤዎችም ተጠብቀው የሚገኙበት ነው፡፡

የ«ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030» ስትራቴጂካዊ ግብ አካል የሆነውን ዘመናዊ የዲጂታይዜሽን ፕሮጀክት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ሰኔ ወር ላይ በይፋ በማስመረቅ ስራ የተጀመረበት እና ያሉንን ታሪካዊ ሀብት ወደ መላው ዓለም በዲጂታል መረብ ለማገናኘት የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራ ተጠናክሮ እየተሰራ እንደሚገኝና ይህንኑ ልምድም ለመመካከር አቻ ተቋማቶች ወደተቋሙ በመምጣት የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበትም እየሆነ መጥቷል፡፡

Share this Post