የሰሜን ሸዋ መዛግብቶችን ለመሠነድ የሚያስችል መግባቢያ ስምምነት ተፈረመ።

ነሐሴ 13/2018 ዓ.ም አዲስ አበባ

የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት የሰሜን ሸዋ መዛግብቶችንና ጥንታውያን የጽሑፍ ቅርሶችን ለመሠነድ የሚያስችል መግባቢያ ስምምነት ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ጋር ተፈርሟል።

የአንድን አካባቢ ማህበረሰብ መዛግብት ለትውልድ ከማሻገርና ከማዳን አንጻር አንድ የመዛግብት ባለሙያ ብቻውን ማዳን እንደማይችል የጠቆሙት የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት ናቸው።

መዛግብትን በመጠብቅ፣ በመንከባከብ እና በማሰባሰብ ሠንዶ ለትውልድ ለማሻገር የአካባቢው ማህበረሰብ የድርሻውን ሊወጣ ይገባልም ብለዋል።

አቶ ሠርፀ አክለውም ከዚህ ሀገራዊ ተቋም ጋር የአንድን ማህበረሰብ መዛግብት ለመሰነድ ተቋሙ የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት እና ድጋፍ ማድረግ የምዘና መረጣ እንዲሁም ዝውውር ስራ በጋራ ለመስራት ለተቋማችን ኃላፊነት በመስጠት ዛሬ የምንፈራረመው ሰነድ ትልቅ አጋርነትን የሚገልጽ ነው ብለዋል።

በመግባቢያ ስምምነቱ ላይ የተገኙት የደብረ ብርሃን የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሲሳይ ሙላቴ ዩኒቨርሲቲው በ1999 ዓ.ም ሲጀምር በመቶዎች መጀመሩንና ዛሬ 20 ዓመቱን ሲያስቆጥር በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን እያሰለጠነ እያስመረቀ እንደሚገኝ ተናግረው

የዩኒቨርሲቲው የትምህርት ሥርዓታችን እውቀት ላይ ብቻ የተመሰረተ በመሆኑ አቅሙን ለማሳደግ የማህበረሰቡን ችግር የሚፈታ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለመጠቀም የሚያስችል በርካታ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው ወደዚህ ሀገራዊ ተቋም ስንመጣ ሠነዶችን መሠነድ የሚችል ተማሪ ለማፍራትና ዘርፉን ለማዘመን ጭምር ነው ብለዋል።

በጥናትና ምርምሩም ዘርፍ ዩኒቨርሲቲው ሲሰማራ ለሀገር መፍትኤ የሚሰጡ እንጂ ሼልፍ ላይ ብቻ መቀመጥ እንደሌለባቸው በማመን ችግር ይፈታሉ ተብለው የተጠኑ የመመረቂያ ጽሑፎች ዲጅታላይዝ ተደርገው በዩኒቨርሲቲው ድህረ ገጽ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሰሜን ሸዋን ቤተመዛግብት ለማቋቋም ዩኒቨርሲቲው የጀመረው የአካባቢውን መዛግብት የማደራጀትና የማሰባሰብ ሥራ ከዚህ ሀገራዊ ተቋም ጋር አብሮ ለመስራትና ተቋሙ ባለሙያዎችን ቦታው ድረስ በመላክ ከዚህ በፊት ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ከበፊቱ በተሻለ ሰርተን የአካባቢውን ሀብት በመሠነድ ጥሩ ጅማሮ በመሆኑ ዛሬ የምንፈራረመው መግባቢያ ሠነድ ተፈራርመን ብቻ የምናስቀምጠው ሳይሆን ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

በመጨረሻም አቶ ሠርፀ በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የተጠኑ እና ጥሩ ውጤት ያገኙና ችግር ፈቺ የሆኑ የጥናት ውጤቶች ወደ አገልግሎቱ በመምጣት ዲጅታላይዝ ተደርገው እንዲቀመጡ እንዲደረጉ የማመቻቸት ስራ ተጠናክሮ እንዲሰራ ጠይቀው የመግባቢያ ስምምነቱ በጋራ ተፈራርመዋል።

Share this Post