"መጻሕፍት የዕውቀት ብርሃን ምንጭ ፀሐዮቻችን ናቸው!"
የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት በአዘጋጅነት የተሳተፈበት ታላቅ የመጻሕፍት አውደ ርዕይ በይፍ ተከፈተ።
የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት እና የንባብ ለህይወት ፕሮጀክት በጋር በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ያዘጋጁት 8ኛው"ንባብ ለህይወት!"ታላቅ የንባብ ሳምንት እና የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ዛሬ ሐምሌ 23/2018 ዓ.ም በይፍ ተከፍቷል።
በአውደ ርዕዩ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት አንድ ሀገር ያለፈውን ታሪክ እንደ አጥንቱ፣የአሁኑን ሁኔታ እንደ ሥጋው፣ የወደፊቱን ተስፋውን ደግሞ እንደ መንፈሱ አድርጎ የሚመለከት ነው።
ይህ አመለካከቱ ጠንካራ ኾኖ እንዲቀጥል የተረት እና የታሪክ፣ የስሜት እና የኃሊና፣የአዲስ እና የአሮጌ፣የወጣት እና የአረጋዊ፣እንዲሁም የእምነት እና የእውቀት መስማማት የግድ ያስፈልገዋል። ብለዋል።
በጥንታውያኑ ግሪካውያን፣ሮማውያን፣ ግበብፃውያን፣በመካከለኛው ምሥራቅ ጥንታውያን ሀገራት በሶሪያ፣በኢራን እና በባግዳድ አሳቢዎች ዘንድ መጻሕፍት መሰብሰብ፣ማቆየት እና ማንበብ የእውቀት ፍለጋ ብቻም እንዳልሆነ ጠቁመው ከከፍተኛ የሰው ልጅ የመንፈሳዊ እና የሞራል ከፍታ ጋር የተያያዘ የተቀደሰ ተግባር ተደርጎም እንደሚወሰድ ተናግረዋል።
ከዛሬ 50 ዓመት በፊት የነበረውን "ያ ትውልድ" የሚባለውን አብዮታዊ ትውልድ ስናስታውስ ንባብ የችግሮች ሁሉ መፍቻ እና የሥልጡን ሰው ኹነኛ መገለጫ ልማድእንደነበርና ሰው በማንበቡ ይከበር እንደነበር ይኸወው ልምድ በቀደመው ጥንካሬው ልክ ባይሆንም እስከ ሚሊኒየሙ መግባት ድረስ ዘልቆ ነበር።ዛሬ ደግሞ በዲጂታል ሥርዓቶች እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) በመታገዝ የሚፈለገው መረጃ በፍጥነት ስለሚገኝ "ከመጻሕፍት እና ከደርሳናት ጋር ጊዜ ማጥፋት አያስፈልግም ወይም አላስፈላጊ ድካም ነው የሚል አደገኛ አዝማሚያ እየታየ እንደሆነም አመላክተዋል።ይሄ ግን የዕውቀት እና የሰው ልጅን ተፈጥሯዊ ቁርኝት ካለመገንዘብ የመጣ የተሳሳተ አመለካካት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
መጻሕፍት የዕውቀት ብርሃን ምንጭ ፀሐዮቻችን ናቸው።ወደ እነርሱ ጠጋ ስንል ኃሊናችን ይበራል።እኛ በምናነብባት በእያንዳንዷ ቅጽበት ለሀገራችን የነገ ተስፋ መልካም መሠረት ይጥላል እና ከማንበብ አንቦዝን በዕውቀት እናንብብ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ስለ ንባብ ባህል፣ታላላቅ መጻሕፍትን አንብቦ ስለመረዳት፣ከንባብ በኋላ ሊኖር ስለሚገባው ጥልቅ ውይይት እንደገና ማሰብ፣ እንደገና መመርመር ጠለቅ ያሉ የንባብ ልምዶችን አስተውሎ ማየት እጅግ የተገባ ተግባር እንደሆነም የተለያዩ የምሁራን አባባሎችን በማጣቀስ ጥልቅ መልዕክት አስተላልፈው አውደ ርዕዩ እስከ ሐምሌ 26/2018 ዓ.ም እንደሚቆ ተነግሯል።
በአውደ ርዕዩ መክፈቻ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት፣የንባብ ለህይወት ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም ከበደ፣ የኢትዮጵያ ሣይንስ አካዳሚ ፕሬዘዳንት ክቡር ፕሮፌሰር በላይ ካሣ፣ የአካዳሚው ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ፣ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል፣በኢትዮጵያ የቁጥር ታሪክ መሠረት የመጀመሪያዋ ሴት የረጅም ልብ ወለድ ደራሲ ወ/ሮ ፀሐይ መላኩ፣አንጋፍ እና ወጣት ደራሲያን ፣የተቋሙ አመራሮችና የሚመለከታቸው ባለሙያዎች፣ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና ክቡራን ታዳምያን ሲገኙበት በዛው መድረክ ጥቁር እንግዳ በመሆን ድምጻዊ ጸሐዬ ዮሐንስ ተገኝቶ ከኢትዮጵያ ልጆች ጋር ስለንባብ ያቀነቀነውን (ማንበብና መጸጻፍ) ስራውን በማቅረብ ታዳሚውን አዝናንቷል።
አውደ ርዕዩን በማስመልከት በኢትዮጵያ ሣይንስ አካዳሚ ፕሬዘዳንት ፕሮፌሰር በላይ ካሣ፣በደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል መልዕክት ሲተላለፍ የተቋሙ የሙዛግብት፣የጽሑፍ ቅርሶች የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ በይፋ ተከፍቶ ለእይታና ለሽያጭ ክፍት ተደርጓል።