የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ታላቅ የዲጂታይዜሽን ፕሮጀክት በይፋ አስጀመረ

ሰኔ 9 ቀን 2018 ዓ.ም አዲስ አበባ
የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር፣የ«ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030»ስትራቴጂካዊ ግብ አካል የሆነውን ዘመናዊ የዲጂታይዜሽን ፕሮጀክት በይፋ አስጀምሯል።
በምረቃ መርሐግብሩ ላይ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት (ወመዘክር) ባለፉት 83 ዓመታት እጅግ ውድ የሆነውን የሀገሪቱን የጽሑፍ ሀብት በብሔራዊ ደረጃ ለመሰብሰብ፣ ለመጠበቅና ለትውልድ ለማሻገር ዕድል ያገኘ ቀዳሚ ተቋም መሆኑን ገልጸው ኢትዮጵያ የጽሑፍ ታሪኳ ጥንታዊና የስልጣኔ ምልክት የታየባት ቀዳሚ ሀገር ብትሆንም፣ የጽሑፍ ሀብቷን በሥርዓት የሚሰበስብ ዘመናዊ ስርዓት በማደራጀት በኩል ግን የታሪኳን ያህል ፈጣን እንዳልነበረች አንስተዋል። ይሁን እንጂ ይህንንም የታሪክ ምዕራፍ የሚቀይርና ያለንን ታሪካዊ ሀብት ወደ መላው ዓለም በዲጂታል መረብ የምታገናኝበትን የቴክኖሎጂ ሽግግር ዛሬ ሰኔ 9 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ ማብሰሯን ገልጸዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ በበኩላቸው፤ በሀገራችን ትናንት በርካታ ታሪካዊ ክንዋኔዎች መፈጸማቸውን፣ ብዙ እውቀቶች መመንጨታቸውንና ድርሳናት መጻፋቸውን አስታውሰዋል። እነዚህ ውድ ሀብቶችና እውቀቶች ዕድሜያቸው ሲገፋ ተበላሽተውና ወድቀው እንዳይቀሩ ወደ ነገ ማሻገር እንደሚገባ ጠቁመው፤ ቴክኖሎጂ የሰጠንን ትልቅ አቅም ተጠቅመን የትናንትን አድሰን ወደ ነገ ማሻገር መቻላችን ትልቅ ስኬት መሆኑን አብራርተዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም ዲጂታል ኢትዮጵያ ስንል ከዛሬና ከወደፊቱ ጉዟችን ባሻገር ወደኋላም ተመልሰን ታሪካችንን በዲጂታል ማዕቀፍ ውስጥ ማካተትን ይጨምራል። ትናንትን በማደስ፣ ዛሬን በማጎልበትና ነገ ደግሞ አዳዲስ እውቀቶችን በተግባር ላይ በማዋል የተሟላ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል ትልቅ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ በበኩላቸው፤ ዛሬ የተበሰረው ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ገልጸዋል። ይህ ተግባር የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን ታላቅ ሀገራዊ ግብ እውን ለማድረግና ለትውልድ የምትተርፍ ሀገር ለመገንባት ትልቅ አበርክቶ ያለው በመሆኑ፣ ፕሮጀክቱ እስከሚጠናቀቅበት ጊዜ ድረስ በተሟላ ቁርጠኝነትና በትጋት እንዲሰራ በአደራ ጭምር አሳስበዋል።
ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በርካታ የመንግሥትና የግል ተቋማት የቴክኖሎጂ ድጋፍ ጥያቄ አቅርበውለት የነበረ ቢሆንም የመረጃ ሀብቶቹን ወደ ዲጂታል የመቀየርን አስቸኳይነት በከፍተኛ ትኩረት በመገንዘብ ለቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ቅድሚያ በመስጠት እውን ያደረገው ፣  ዓለምአቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ እጅግ ዘመናዊ የዲጂታይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን፣ ሶፍትዌሮችንና የሀርድዌር ሥርዓቶችን ያካተተ፣ ከእነዚህም መካከል ለጥንታዊ መጻሕፍት ልዩ ጥንቃቄ የሚያደርጉ ዘመናዊ የመጻሕፍት ስካነሮች፣ የሰነድና የካርታ መዛግብት ስካነሮች እንዲሁም የተደራጁ የኮምፒውተር አውታረ-መረብ መሰረተ-ልማቶች በአጠቃላይ 792,422 (ሰባት መቶ ዘጠና ሁለት ሺህ አራት መቶ ሀያ ሁለት) የአሜሪካ ዶላር ወይም በወቅታዊ ምንዛሬ 126,787,520 (መቶ ሀያ ስድስት ሚሊዮን ሰባት መቶ ሰማኒያ ሰባት ሺህ አምስት መቶ ሀያ) የኢትዮጵያ ብር ወጪ የተደረገበት ነው።
ይህ የተዘረጋው ቴክኖሎጂ በተቋሙ ውስጥ ያሉትን የጽሑፍ ሀብቶች በሙሉ አቅም ወደ ዲጂታል ለመቀየር የሚያስችል ቋሚ መሰረተ-ልማት ሲሆን፤ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በተያዘው በዚህ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ 20 ሚሊዮን ገጾችን ወደ ዲጂታል የመቀየር ሥራ በፓይለት ፕሮጀክትነት በተሳካ ሁኔታ ለማጠናቀቅ ዕቅድ ተይዟል።

Share this Post