የሰኞ ንጋት «እንገናኝ እንሰናኝ» መድረክ፦ ትስስራችንን እናጠንክር፣ በርኅራኄ እንተያይ
ሰኔ 1/ 2018 ዓ.ም አዲስ አበባ
በ3ኛው ዙር«እንገናኝ እንሰናኝ»የሰኞ ንጋት መድረክ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት «ትስስራችንን እናጠንክር፣በርኅራኄ እንተያይ»በሚል መሪ ሐሳብ ለተቋሙ ባልደረቦች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በመድረኩ ላይ አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት እንደገለጹት፣ሕዝቦች በተሳሰረ ማንነትና በትብብር አብረው አገርን እንደሚገነቡ እንጂ አንድ ወገን ብቻውን ቆሞ አገር ማቅናት እንደማይችል አስገንዝበዋል። ይህንን እውነት ወደ ተቋማዊ አሠራር ስናመጣውም፣ በተቋሙ ውስጥ ቀድሞ የነበረውም ሆነ ዘግይቶ የተቀላቀለው ሠራተኛ ሁሉ «ተቋም» በሚለው የጋራ ጥላ ሥር የየራሱን አሻራ እንደሚያሳርፍና ለጋራ ስኬት እንደሚሠራ አብራርተዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ በትብብርና አብሮነት ጉዞ ውስጥ ወሳኝ የሆኑትን Apathy (ግዴለሽነት)፣ Sympathy (አዘኔታ) እና Empathy (የስሜት ተካፋይነት) የተሰኙ ሦስት ቁልፍ ፅንሰ-ሐሳቦችን በጥልቀት ዳስሰዋል።የቃላቱ ትርጉምና በተቋማዊ ግንባታ ላይ ያላቸው ሚናም በመድረኩ ላይ በሚከተለው መልኩ ተብራርቷል፦
Apathy (ግዴለሽነት)፦ የሌሎችን ሁኔታ፣ችግርም ሆነ ደስታ ምንም ዓይነት ስሜት ሳይሰጡ በቸልተኝነት ማለፍ ሲሆን፣ ይህ ዓይነቱ አመለካከት የተቋምን ትስስር የሚጎዳ እንደሆነ ተገልጿል።
Sympathy (አዘኔታ)፦ የሌላውን ሰው ችግር ወይም ስቃይ ከውጭ ሆኖ ማዘንና «አይዞህ» ማለት ሲሆን፣ ምንም እንኳ መልካም ቢሆንም ብቻውን ግን በቂ እንዳልሆነ ተብራርቷል።
Empathy (የስሜት ተካፋይነት)፦ እራስን በሌላው ሰው ቦታ ተክቶ፣ ያ ሰው ያጋጠመውን ችግር በእራስ ላይ እንደደረሰ አድርጎ የመረዳት ጥበብ ነው።
አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት አክለውም፣ «Empathy (የስሜት ተካፋይነት) ማለት የኛን ዕርዳታ ወደሚፈልግ ሰው አንድ እርምጃ ጠጋ ማለትን፣በዚያ ሰው ጫማ ውስጥ ሆኖ የማሰብ ጥበብ ነው» ብለዋል።
በመጨረሻም፣የእያንዳንዱ ሠራተኛ አዎንታዊ አስተዋጽዖ በሌላው ላይ እየተጨመረ ለሚገነባው አገርና ተቋም፣እርስ በርስ የመተሳሰር እና በርኅራኄ የመተያየት ክህሎትን ማዳበር እንደሚገባ አጽንዖት ተሰጥቶበታል።በተለይም በሕዝብ አገልግሎት (Public Service) ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የተቋሙ ባልደረቦች፣እርስ በርስ ክህሎትን የመጋራትና የመደጋገፍ (የመተናነጽ) ባህልን ይበልጥ ሊያጠነክሩ እንደሚገባ በማሳሰብ መድረኩ ተጠናቋል።