ለአሥር ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የነበረው ታሪካዊ የሙዚቃ ቅርስ አውደ ርዕይ ተጠናቀቀ፡፡
ከዘጠና አመታት በፊት በነበሩ አዝማሪዎች እና የባህል ሙዚቃ ተጫዋቾች የተቀረጹ የሙዚቃ ስራዎች ከጥንታዊ ፎቶ ግራፎችና ከሙዚቃዎቹ ታሪክ ጋር ተካቶ የተዘጋጀው ልዩ አውደ ርዕይ ተጠናቀቀ።
በኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ከሚያዝያ 23/2018 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ አሥር ቀናት ለተመልካች ክፍት የነበረው ላለፉት ዘጠኝ አስርት ዓመታት በዝምታ ተውጠው የቆዩት የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅርሶች አውደ ርዕይ በስኬት ተጠናቋል።
አውደ ርዕይ በጣሊያን ወረራ ወቅት (ከ1928-1933 ዓ.ም) በአዲስ አበባ በኮሎምቢያ ሪከርድስ አማካኝነት ተቀርጸው የነበሩ በዘመናዊ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ታድሰው የቀረቡ ከ350 በላይ ብርቅዬ የሙዚቃ ቅጂዎች ነበሩ፡፡
የተዘጋጀውን አውደ ርዕይ በተመለከተ አስተያየታቸውን የሰጡት ጎብኚ ሳሙኤል ወርቅዬ እና ደሳለኝ በጋሻው እንዲህ ዓይነቱ አውደ ርዕይ ተዘጋጅቶ በሰው ሀገር ውስጥ የሀገራችን ንብረት ተጠብቆ ዛሬ በዚህ መልክ አውደ ርዕይ ተዘጋጅቶ እንዲታወቅ ማድረጋችሁ "እጅግ በጣም ጥሩ ነው በዚሁ በመቀጠል ለተተኪው ትውልድ የሚሆኑ ስራዎች የተሠሩበት የሸክላ ማጫወቻ ዘፈኖች በዲጂታል አድርጎ በማሰራጨት ለዜጎች በቀላሉ እንዲሰሙ ለማድረግ ያደረጋችሁት ጥረት እጅግ በጣም የሚያስመሰግን በመሆኑ በዚሁ ቀጥሉ በተጨማሪም ታሪኮችን በፎቶግራፍ በማሳየት መልካም ሥራ በመሥራት ላይ እንዳላችሁ ይህ ምስክር ነው" በማለት ምስጋናቸውን ሰጥተዋል፡፡
የኢንስፓርክ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ሚውዚኮሎጂስት ጂያንፓኦሎ ኪሪያኮ Gianpaolo Chiaraco እነዚህን ከዘጠና አመታት በፊት በኮሎምቢያ ሪከርድስ የተቀዱ ስራዎችን በማሰባሰብና በማደራጀት ከኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ጋር በመቀናጀት በልዩ ሁኔታ ለአውደ ርዕይ እንዲበቃና ለሕዝብ ተደራሽ በማድረጋቸው እንደሀገር ምሥጋናችን ከፍ ያለ ነው፡፡
አውደ ርዕዩን በኦንላይን (በበይነ መረብ) የጎበኙትን ሳይጨምር በአካል በተቋሙ በመገኘት ከአራት ሺህ በላይ ጎብኚዎች ጎብኝተውታል፡፡