የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመፃሕፍት አገልግሎት የሰኞ ንጋት“እንገናኝ እንሰናኝ”መድረክ አካሄደ፡፡
ግንቦት 03/2018 ዓ.ም አዲስ አበባ
የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመፃሕፍት አገልግሎት የመጀመሪያውን የሰኞ ንጋት“እንገናኝ እንሰናኝ”መድረክ አካሄደ፡፡
“እንገናኝ እንሰናኝ”የተሰኘው መድረክ የባለሙያዎችን ትስስር ለማጠናከር እና የተቋሙን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማፋጠን ታልሞ የተዘጋጀው የሰኞ ንጋት የየኹለት ሳምንት መርሐ ግብር የመጀመሪያ መድረክ በብላቴን ጌታ ህሩይ ወልደሥላሴ አዳራሽ ተካሂዷል።
ከአዲስ አበባ መስተዳድርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ ተቋማት በመነሳት በተቋሙ መልክና አቋም የተቀረጸ መልካም ተሞክሮ እንደሆነ የገለጹት የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት“ሁላችንም የየራሳችን ልዩነቶች ቢኖሩንም ሃሳቦቻችንን በጥበብ በማገናኘት አንድ በሚያደርገን ተቋም ስር እንድንኖር ያስችለናል”በማለት “እንገናኝ እንሰናኝ” በየሁለት ሳምንቱ የሚቀርብ የሰኞ ንጋት መርሃ-ግብርን በይፋ አስጀምረዋል።
“ናሂሊ”የተሰኘውን መጽሐፍ በዚሁ አዳራሽ አስመርቀው ለንባብ ያበቁት ደራሲ ናትናኤል ከበደ “የቱ ጋር ነው የተለያየነው?” በሚል ርዕስ ሰፊ ገለጻ ለታዳሚያን አጋርተዋል።
ደራሲው ያቀረቡት ዳሰሳ መነሻውን በኦሮሚያ ክልል አድርጎ በጥናትና ምርምር በኢትኖግራፊክ የልብ-ወለድ አጻጻፍ ስልት የከተቡትን “ናሂሊ” የተሰኘ መጽሐፋቸውን መሰረት ያደረገ ሲሆን “እርግጥ ነው ቋንቋችን ይለያያል የፖለቲካ አስተሳሰባችንም እንደዛው ወደ ማህበረሰባችን ወርጄ ሳየው ግን እጅጉን አንድ ነን፤ እንዋደዳለን፤ አንደበታችን ቢለያይም ነፍሳችን አንድ ነው” የሚል መደምደሚያ ያለውን ሃሳብ የያዘ ነው።
ይህ መድረክ የሃሳብ ተግባቦትን በሚያጎልብትና ጥሩ የስራ መነቃቃትን በሚፈጥር መልኩ ባህል ሆኖ እንደሚቀጥል የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት አመላክተዋል።