ታሪካዊው የሙዚቃ ቅርስ አውደርዕይ ተካሄደ።
ሚያዝያ 29/2018ዓ.ም አዲስ አበባ
ላለፉት ዘጠኝ አስርት ዓመታት በዝምታ ተውጠው የቆዩት የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅርሶች ዛሬ በኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት በደመቀ ሁኔታ ለድምጫ አውደ ርዕይ በቅተዋል።
ይህ አውደርዕይ በጣሊያን ወረራ ወቅት (ከ1928-1933 ዓ.ም) በአዲስ አበባ በኮሎምቢያ ሪከርድስ አማካኝነት ተቀርጸው የነበሩ ከ350 በላይ ብርቅዬ የሙዚቃ ቅጂዎች በዘመናዊ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ታድሰው ለታዳሚ የቀረቡበት ነው።
የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት ዕለቱ ለዘጠኝ አስርት ዓመታት ተቀብሮ የቆየ የታሪክ ቅርስ ትንሳኤ የሚበሰርበትና የታሪክ ስብርባሪዎች ሙሉ ሥዕል የታየበት መሆኑን ለኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ ለሙዚቃ አፍቃርያንና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አብስረዋል።
በወቅቱ ቅጂዎቹን ከያዘው ከኮሎምቢያ ሪከርድስ በስተቀር ሙሉ ስብስቦቹ በማንኛውም ተቋም በማይገኙበት ሁኔታ በጥልቅ ጥናትና ምርምር አሰባስበው ለኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት በስጦታ ያበረከቱት የቱሪን ዩኒቨርሲቲ ሚውዚኮሎጂስት ፕሮፌሰር Gianpaolo Chiaraco ናቸው።ፕሮፌሰሩ በንግግራቸው "ሙዚቃ ታሪክን ይነግረናል፤ ከነዚህ ድንቅ ስብስቦችም ታሪክን እንማራለን" ብለዋል።
ተቋሙ በውጭ ሀገር የሚገኙ ማህደሮችን በማፈላለግ የድምፅ ቅርሶችን ወደ ሀገር ቤት በመመለስና ለትውልድ እንዲተላለፉ በማድረግ በወቅቱ የነበረውን የታሪክ ስብራት ወደ ታላቅ የባህልና የኪነ-ጥበብ ምርምር እንዲቀየር ላደረጉት ለጣሊያናዊው ፕሮፌሰር Gianpaolo Chiaraco የምስጋና የምስክር ወረቀት አበርክቶላቸዋል።
የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት እነዚህን በዋጋ የማይተመኑ ቅርሶች በቋሚነት እንዲጠበቁና ለጥናትና ምርምር ክፍት እንዲሆኑ የሚያደርግ መሆኑንም አስታውቋል።