"የንባብ ባህል ለትምህርት ጥራት!"በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው የሕጻናት የንባብ ቀን በስኬት ተጠናቀቀ።
ሚያዝያ 22/ 2018ዓ.ም
አዲስ አበባ
የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት በመላው ኢትዮጵያ ሲካሄድ የቆየው የንባብ ባህል ማዳበር ንቅናቄ አካል የሆነ የህፃናት የንባብ ቀን "የንባብ ባህል ለትምህርት ጥራት!"በሚል መሪ ቃል በተቋሙ ቅጥር ግቢ ውስጥ በሕጻናት ቤተ መጻሕፍት በደመቀ ሁኔታ አካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ከሜጀር ጀነራል ኃያሎም አርአያ እና ከዕድገት በህብረት ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል የሚገኙ ተማሪዎች የተሳተፉበት ነበር።
ተማሪዎች ዕውቀትን የሚያገኙባቸውን መንገዶች በማብራራት ተቋሙ ለንባብና የትውልድን አዕምሮ ለማበልጸግ እንደሚሠራ እንዲሁም ማንበብ ለምትፈልጉ በሩ ክፍት ነው ሲሉ የተቋሙ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አባተ ካሳው በመክፈቻ ንግግራቸው ተናግረዋል፡፡
የንባብ ክበባት በት/ቤቶች መመስረት ለሀገር ችግር መፍትኤ የሚሆን በዕውቀት የዳበረ ትውልድ ለመፍጠር ያለውን ፋይዳ የአብያተ መጻሕፍት አገልግሎት መሪ ስራ አስፈጻሚ ተወካይ ወ/ሮ ቅድስት ጌታቸው ለተማሪዎቹ ገለጻ አድርገዋል፡፡
በዚሁ መርሐ ግብር የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሀገሬ መኮንን የቀድሞ የመምህርነት ሙያ ጉዟቸውንና የልጆች አስተዳደግ ልምዳቸውን ለተማሪዎችና ለመምህራን አካፍለዋል።
ትምህርትና ንባብ የማይለያዩ መሆናቸውን የተናገሩት ትምህርት ቤቶቹን ወክለው የመጡ መምህራን “ተማሪ ሰነፍ አይደለም!” የማንበብ ፍላጎት አለው፤ ነገር ግን መንገዱን የሚያሳየው ይፈልጋል ተቋማችሁም ለሀገር የሚሰራና ከትምህርት ጎን የቆመ በመሆኑ በቀጣይ ለዚሁ ተግባር የሚያግዝ ስልጥናና ሁነት በት/ቤት እንዲዘጋጅ የአብረን እንስራ ጥሪ አቅርበዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ለተሳተፉ ት/ቤቶች ተቋሙ ያዘጋጀውን የምስክር ወረቀት የአብያተ መዛግብትና ያብያተ መጻሕፍት ስልጠናና ምክር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ መኮንን ከፍያለ እና የአብያተ መጻሕፍት መረጃ ሀብቶች አስተዳደር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ስለሺ ሽፈራው ት/ቤቱን ወክለው ለመጡ መምህራን አስረክበዋል።
ዝግጅቱ በትምህርት አዘል ተረቶች፣በጥያቄና መልስ፣በመጽሐፍት ሽልማት እንዲሁም በጉብኝት የታጀበና የተማሪዎች ንቁ ተሳትፎ የታየበት ነበር።