ታላቅ የንባብ ሳምንት መርሐግብር በባህርዳር ተጀመረ

የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ባህል ቱሪዝም ቢሮ እና ከባህርዳር ዩንቨርሲቲ ጋር በመተባበር "መጻሕፍት የዕውቀት ጮራ፤ መዛግብት የታሪክ አሻራ" በሚል መሪ ቃል ዓውደ ርዕይ፣ የመጻሕፍት ዓውደ ትዕይንትና ሽያጭ እና የፓናል ውይይት የንባብ ሳምንት በባህር ዳር ከተማ ቅዳሜ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓም በይፋ ተጀምሯል።
የንባብ ሳምንቱ መክፈቻ መርሐግብር ዓውደ ርዕዩ በተዘጋጀበት የቀድሞው ግዮን ሆቴል አካባቢ ሲከፈት የሙሉአለም ባህል ማዕከል ኃላፊ አቶ ገ/ማርያም ይርጋ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ፣ የክልሉ ባህል ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ መኮንን የመክፈቻ ንግግር እና የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ የንባብ ሳምንቱን ዓላማ አስመልክቶ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ ክቡራን እንግዶቹ በጋራ የመክፈቻ ሪቫኑን በመቁረጥ አውደርዕዩን ለህዝብ ክፍት አድርገዋል።
በመርሐግብሩ በገጣሚያን ዮሐንስ ገ/መድህን እና ፍሬዘር ዘውዴ ግጥም የቀረበ ሲሆን በግሽ አባይ የባህል ቡድን ውዝዋዜና ሙዚቃ ቀርቧል።
በዚህ መርሐግብር የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ለዳንግላ 1ኛና 2ተኛ ደረጃ ት/ቤቶች፣ ለዳንግላ ማረሚያ ቤት እና ለዳንግላ የህዝብ ቤተመጽሐፍት፣ ለባህር ዳር 1ኛና 2ተኛ ደረጃ ት/ቤቶች፣ ለባህር ዳር የህዝብ ቤተመጽሐፍት፣ ለባህር ዳር ማረሚያ ቤት ፣ ለመርጦ ለማርያም የህዝብ ቤተመጽሐፍት፣ ለደብረ ወርቅ የህዝብ ቤተመጽሐፍት፣ ለሉማሜ የህዝብ ቤተመጽሐፍት፣ ለቀይት የህዝብ ቤተመጽሐፍት፣ ለአዴት የህዝብ ቤተመጽሐፍት እና ለም/ጎ 2ተኛ ደረጃ ት/ቤት በድምሩ 10,600 (አስር ሺ ስድስት መቶ ) መጻሕፍት በገንዘብ ሲተመን  1,670,082 ብር (አንድ ሚሊዮን ስድስት መቶ ሰባ ሺህ ሰማኒያ ሁለት ብር ከዘጠኝ ሳንቲም) ወጪ በማድረግ በስጦታነት እንደሚያበረክት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር በመርሐግብሩ ላይ አሳውቀዋል።

Share this Post