ለተቋሙ የምስጋና ወረቀት ተሰጠ፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ከአርሲ ዩኒቨርሲቲ፣ ከጢዮ ወረዳ አስተዳደር እና ከጢዮ ወረዳ ት/ቤቶች ጽ/ቤት ጋር በመተባበር "የንባብ ባህል ለትምህርት ጥራት" በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው የንባብ ሳምንት፣ የፖናል ውይይትና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በአሰላ ከተማ ተካሔደ።

በመክፈቻ መርሐግብሩም የሀገር ሽማግሌዎች፤ አባገዳዎች እና ሀዳ ስንቄዎች፣ የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አባተ ካሳው፣ የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕረዝዳንት ዶ/ር ሙስጠፍ ባቲ፣  የአርሲ ዩኒቨርሲቲ  የጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር ሐይሉ ፍቃዱ፣ የጢዮ ወረዳ የብልፅግና ፓርቲ ሀላፊና የጢዮ ወረዳ ተወካይ አስተዳደር  አቶ ሙሀመድ አማን፣ የአርሲ ዞን ት/ት መምሪያ ኃላፊ አቶ አህመድ ሁሴን  እና የጢዮ ወረዳ  ት/ት ቤቶች ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ አበራሽ በየነ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።

አቶ አባተ ካሳው በመልዕክታቸው "ከልማት ሁሉ የላቀውን ድርሻ የሚወስደው የሰው ልጅ የአእምሮ ልማት ነው፤ ለዚህም ክቡር ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ በመጀመርያው የልማት እንቅስቃሴያቸው ለቤተ-መጽሐፍት ትኩረት እንደሰጡ በየደረጃው ይህንን ፈለግ የሚከተል አመራር ያስፈልገናል" ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት በጢዩ ወረዳ ለሚገኙ 9 አንደኛ እና 4 ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች እንዲሁም ለአስላ  ማረሚያ ቤት በጥቅሉ  1,069,698 ብር ዋጋ ያላቸው  3543 መጻሕፍት በስጦታ አበርክቷል።

ስጦታውንም የተቋሙ የመረጃ ሀብቶች ማሰባሰብና ማደራጀት የስራ ክፍል መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ስለሺ ሽፈራው ለጢዮ ወረዳ የብልፅግና ፓርቲ ሀላፊና የጢዮ ወረዳ ተወካይ አስተዳደር  አቶ ሙሀመድ አማን፣ ለአርሲ ዞን ት/ት መምሪያ ኃላፊ አቶ አህመድ ሁሴን  እና ለጢዮ ወረዳ  ት/ት ቤቶች ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ አበራሽ በየነ አስረክበዋል።

ለዚህም ተቋሙ ከአርሲ ዞን ጢዮ ወረዳ ት/ቤቶች ጽ/ቤት የምስጋና ወረቀት ተበርክቶለታል፡፡

መርሀ ግብሩ "አቤ ከቤ ከአሰላ" በክብር እንግዳነት ተገኝተው በአሰላ ከተማ ቤተ-መጽሐፍት ለመገንባት ዕቅድ እንዳላቸው  ያደመጥንበት ነበር።

"የንባብ ባህል ለትምህርት ጥራት" በሚል መሪ ቃል በአሰላ ከተማ የተዘጋጀው የንባብ ሳምንት፣  የፓናል ውይይትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መድረክ አካል የሆነው መርሀ ግብር በአስላ ማረሚያ ቤትም የተካሔደ ሲሆን  ለማረሚያ ቤቱ 113,940 ብር ዋጋ ያላቸው 340 መጻሕፍት የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት የመረጃ ሀብቶች ማሰባሰብና ማደራጀት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ስለሺ ሽፈራው ለአስላ ማረሚያ ቤት ኃላፊ ኮማንደር አበራ ገለታ በስጦታ አበርክተዋል ።

የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ - መጻሕፍት አገልግሎት የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አባተ ካሳው ባስተላለፉት መልዕክት "ሰዎች አገልግል ይዘው እንደሚጠይቋችሁ እኛም መጽሐፍ ይዘን ልንጠይቃችሁ መጥተናል" በማለት ስለ መርሀ ግብሩ ዓላማ ለታዳምያን አብራርተዋል፡፡

የደራስያን ተሞክሮም በደራሲና ጋዜጠኛ ኢሳያስ ሆርዶፋ፣ በደራሲ ሊዲያ ተስፋዬ እና በመምህርና ተርጓሚ ቁልቁሉ ኢጆ ጋዲሳ ቀርቧል::

ይህ ሁነት የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ከአርሲ ዩኒቨርሲቲ፣ ከጢዮ ወረዳ አስተዳደርና ከጢዮ ወረዳ ት/ቤቶች ጽ/ቤት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።

Share this Post