ስምንተኛው አገር አቀፍ የግእዝ ጉባዔ ተካሔደ

የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ከወሎ ዩኒቨርሲቲ እና ከአማራ ክልል ባህል ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር ስምንተኛውን አገር አቀፍ የግእዝ  ጉባዔ "ናዝልፍ ኀበ አንብቦተ መጻሕፍተ ግእዝ" በሚል መሪ ቃል በደሴ ከተማ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ቀን ጉባዔውን ሚያዝያ 28/2017 ዓ.ም አካሂዷል።

በጉባዔው የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ፣ዶ/ር አወል ሱለይማን የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት፣የወሎ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚ ጉዳዮች ም/ፕሬዘዳንት ዶ/ር ብርሃን አስማሜ፣ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዶ/ር አድገ፣ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በግዕዝ ቋንቋና ሥነ ጽሑፎች ላይ ጥናት ያደረጉ ምሁራንና ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ከአገልግሎቱ የጽ/ቤት ኃላፊው አቶ አባተ ካሳው እና የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈውበታል።

በጉባዔው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በወሎ ዩኒቨርሲቲ ም/ፕሬዘዳንት  በዶ/ር ብርሃን አስማሜ ሲደረግ በመልዕክታቸው የግዕዝ ቋንቋ ፋይዳ እና የቋንቋውን መሠረቱ ጥንት  ሲሆን የራሱ ፊደል ያለው የሥነ ጽሑፍ ቋንቋ፤ የፍልስፍና፣ ለመድኃኒት ቅመማ የሚያገለግል በውጭ ሀገር ሳይቀር በዶክተሬት ድግሪ ማስተርስ እየተሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡም ግዕዝ ጥንታዊ የሥነ ጽሑፍ ቋንቋ እንደሆነ ተናግረው የሥነ ጽሑፍ ቋንቋ ያስባለው ከራሳችን ምናብና ሃሳብ የተዋለዱ ርዕሰ ጉዳዩች እንደተጻፉ ለዚህም ማሳያነት ዜና መዋዕለን ብናይ  አንድ የሀገራችን ንጉስ የየዕለት እንቅስቃሴዎች  በቋንቋው  ሰፍረውበት እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በማከልም አቶ ይኩኖአምላክ የዛሬው ጉባዔ ይህንን ሁሉ ሀብት ይዘን ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት የምንጥርበት ጉባዔ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

በመቀጠልም በዶ/ር ዩሐንስ አድገ የግዕዝ ሚና በአካዳሚው ዓለም፤በመ/ር ላዕከማርያም ብርሃኑ የንባብ ባህል በግዕዝ ድርሳናት ውስጥ፤መ/ር ጸዳለ አዲሱ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ንባበ ግዕዝን በድግግሞሽ የመማር ብልሃት አተገባበርና የመምህር ምጋቤ ምላሽ፤በመ/ር ደረጀ ሣህሌ ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የግእዝ መንፈሣዊ ድርሰቶች እና ምንባብ በማስመልከት ከአባ ጊዩርጊስ ዘጋስጫ ውስን ሥነ ጽሑፎች፤በዶ/ር መስፍን ፍቃዴ ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የአብነት ትምህርት የአስተምሮ ሥርዓት ጥበባዊ ፋይዳዎች እና ማህበራዊ እሴቶች በምሥራቅ ጎጃም ዞን በጎዛምን ወረዳ ማሳያነት፤ከኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ በመ/ር ኢያሱ በሬንቶ ጥበበ ምግባረ ሠናይ እና ሰው መሆን በግዕዝ ሥነ ጽሑፍ ማር ይስሐቅ ላይ የተደረጉ ፍልስፍናዊ ትንታኔ ዙሪያ ጥናታዊ ጽሑፎች ሲቀርቡ ከጥናታዊ ጽሑፎቹ በተጨማሪ በሊቃውንቱ ቅኔ የተዘረፈበትና ድጓ መዝሙሮች በመቅረብ ተዛታፊውን አስደምመዋል።

በመጨረሻም የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተርና የወሎ ዩኒቨርስቲ ፕሬዘዳንት ግዕዝን በተመለከተ ስራዎችን በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ ሲፈራረሙ በቀረቡ ጥናታዊ ጽሑፎች ከተሳታፊውች ጥያቄ፣ሃሳብ አስተያየት ተሰንዝሮ ምላሽ ለሚሹት ከአቅራቢዎቹ ምላሽ በመስጠት ሃሳብና አስተያየቶቹን ለጽሑፋቸው ማዳበሪያነት እንደሚጠቀሙት በመጠቆም የመጀመሪያ ቀን የግዕዝ ጉባዔ ውሎ ተጠናቋል።

Share this Post